በትራፊክ አደጋ የሦስት ሰዎች ህይወት አለፈ

61
አዳማ ግንቦት20/2010 በምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የሦስት ሰዎች ህይወት ወዲያውኑ ሲያልፍ በሁለት ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን የዞኑ ፖሊስ ገለፀ ። የዞኑ ፖሊስ የህዝብ ግንኝነት ኃላፊ ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ እንደገለፁት አደጋው የደረሰው ትናንት ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ላይ ቲማቲም ጭኖ ከአዳማ ወደ ድሬዳዋ ሲጓዝ የነበረ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 አአ 05654 አይሱዙ የጭነት መኪና አሸዋ ጭኖ ከመተሀራ ወደ አዳማ ሲጓዝ ከነበረ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 ኢት70539 ሲኖትራክ ተሽከርካሪ ጋር በመጋጨታቸው ነው  ። ተሽከርካሪዎቹ ፈንታሌ ወረዳ ጡጡቲ ቀበሌ ልዩ ስሞ ሃያ ቦሎ በተባለ ስፍራ በአጋጠማቸው ግጭት ምክንያት በአይሱዙው የነበሩ ሾፌሩን ጨምሮ ሶስት ሰዎች ወዲያውኑ ህይወታቸው አልፏል፡፡ የሲኖትራኩ ሾፌርና የአይሱዚው ረዳት ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ''ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሁለቱ ሰዎች በአዳማ ሆስፒታል በህክምና ላይ ሲሆኑ የሟቾቹ አስከሬንም በሆስፒታሉ ይገኛል'' ብለዋል ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ ። በአደጋው ከደረሰው የህይወት መጥፋትና ከባድ የአካል ጉዳት በተጨማሪ 500 ሺህ ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል ። የአደጋው መንስኤ በጠመዝማዛ መንገድ ላይ ቅድሚያ ባለመስጠትና ከመጠን በላይ ፍጥነት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ወቅቱ ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አሽከርካሪዎች ከጉዞ በፊት የተሽከርካሪያቸውን ደህንነት ማረጋገጥና የትራፊክ ህግና ደንብ አክብረው ማሽከርከር እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም