የመጀመሪያው የመካንነት ህክምና ማዕከል ተመረቀ

233

አዲስ አበባ የካቲት 3/2011 ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የተቀናጀ የመካንነት ህክምና የሚሰጠውን የስነ-ተዋልዶ ህክምና ማዕከል መርቀው ከፈቱ።

ማዕከሉ ከሴቷ እንቁላል ከወንዱ ዘር በመውሰድ ከማህፀን ውጪ ልጅ እንዲፈጠር በማድረግ መልሶ በሴቷ ማህጸን ውስጥ ጽንሱን የማስቀመጥ በቴክኖሎጂ የታገዘ የህክምና አገልግሎት የሚሰጥበት ነው።

ማዕከሉን መርቀው የከፈቱት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እንደተናገሩት የማዕከሉ መቋቋም አገልግሎት ፈልገው ሲንገላቱ የነበሩ ሰዎችን ችግር ለመፍታት ይረዳል።

የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ጤናማና ቤተሰቧን የምትመጥን ሴት መፍጠር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ማዕከሉን ለማጠናከር ሁሉም በትብብር እንዲሰራ በመጠየቅ ወደ ማዕከሉ የሚመጡ ጥንዶች ምኞታቸው እንዲሳካ ተመኝተዋል።

የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን በበኩላቸው ቤተሰብ መውለድና ማዘግየት ሲፈልጉ እንደየምርጫቸው አገልግሎት መስጠት የጤና ሚኒስቴር ዓላማ ነው ብለዋል።

እስካሁን የማዋለድና መውለድን ማዘግየት ለሚፈልጉ ቤተሰቦች የወሊድ መቆጣጠሪያ አገልግሎት በመላው አገሪቱ እየተሰጠ የነበረ ቢሆንም መውለድ ለማይችሉ አገልግሎቱ አልነበረም።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ የማዕከሉ መከፈት በኢትዮጵያ መውለድ የማይችሉ አምስት ሚሊዮን ለሚደርሱ ጥንዶች አገልግሎት በመስጠት የተሟላ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት እንዲኖር ያደርጋል።

ማዕከሉ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም የህክምና ኮሌጅ ስር የሚገኝ ነው።

በኮሌጁ የማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስትና የማዕከሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ቶማስ መኩሪያ ለኢዜአ እንዳሉት ማዕከሉ የተቀናጀ የመካንነት ምርመራ ለመስጠት የተከፈተ ነው።

ቀደም ሲል በግል የጤና ተቋማት እንጂ በመንግስት ደረጃ የተቀናጀ የመካንነት ህክምና አገልግሎት እንዳልነበረ በመግለጽ መንግስት አገልግሎቱን ሊጀምር መሆኑን ሰምተው በቅዱስ ጳውሎስ ከታዩት ከአንድ ሺህ 700 በላይ የመካንነት ችግር ያለባቸው ጥንዶች 500 የሚሆኑት አገልግሎቱን እየጠበቁ ይገኛሉ።

በመሆኑም ማዕከሉ በቀጣዩ ዓመት ከስድስት ወር አገልግሎት መስጠት የሚችለው 500 እና ከዛ በታች በመሆኑ አቅም ያላቸው ሌሎች አማራጮችን እንዲጠቀሙ መክረዋል።

ኮሌጁ የህክምና ማዕከሉን ማቋቋም ያስፈለገው በተፈጥሮ መንገድ ልጅ መውለድ የማይችሉ ሰዎችን ቁጥር ከግምት በማስገባትና ለመርዳት መሆኑን አስረድተዋል።    

ማዕከሉ በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ 22 ማዞሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኝ ሲሆን 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ሆኖበታል ነው።

በታዳጊ አገሮች በተፈጥሮ መንገድ ልጅ መውለድ የማይችሉ ጥንዶች ከ10 እስከ 15 በመቶ እንደሚሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም