የፍልስጤም መንግስት አፍሪካን የሚጎዳ አክራሪነትና የሽብር ድርጊትን ያወግዛል - መሐሙድ አባስ

71

አዲስ አበባ የካቲት 3/2011 የፍልስጤም መንግስት በአፍሪካ ጉዳት የሚያደርስ አክራሪነትና የሽብር ድርጊትን እንደሚያወግዝ የፍልስጤም ፕሬዝዳንት መሐሙድ አባስ ተናገሩ።

ፕሬዝዳንቱ በአፍሪካ ህብረት 32ኛው የመሪዎች ጉባዔ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ በቅርቡ በኬንያ የደረሰው የሽብር ጥቃት የሚወገዝ ድርጊት ነው።

መንግስታቸው የአፍሪካ ከተሞች ላይ ጉዳት የሚያስከትል ማንኛውም አይነት የአክራሪነትና የሽብርተኝነት ድርጊትን አጥብቆ የሚቃወም መሆኑንም ተናግረዋል።

በበርካታ የአፍሪካ አገሮች እየተካሄደ ያለው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጥ የሚደነቅ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ሰላማዊ በሆነ መንገድ የስልጣን ሽግግር መከናወኑና በምርጫ ወደ ሃላፊነት መምጣት መጀመሩ ለአህጉሪቱ የዴሞክራሲ ግንባታ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው በኢትዮጵያ በተከናወነው ለውጥ ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት በመምጣታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ የተካሄደው አብዮት ለመጪው የኢትዮጵያ ዘመን ተስፋ የፈነጠቀ ነው በማለትም በተመሳሳይ፤ በሩዋንዳ ፓርላማና በሚኒስትሮች ካቢኔ ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የተወሰደውን እርምጃ አድንቀዋል።

የፍልስጤም መንግስት ከአፍሪካ አገሮች ጋር በትብብርና በአጋርነት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

ፍልስጤም ከእስራኤል ጋር ያላትን የሻከረ ግንኙነት በተመለከተ በማንኛውም የድርድር ሂደት ውስጥ አሜሪካ እንድትገባ እንደማይፈልጉ ፕሬዝዳንት መሐሙድ አባስ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በመክፈቻው ላይ ንግግር ያደረጉት የአረብ ሊግ ዋና ጸሀፊ አህመድ አቡል-ጌት በበኩላቸው የአረብ ሊግ አባል አገሮች ከአፍሪካ ህብረት አባል አገሮች ጋር በመቀራረብ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በሊቢያ ያለውን ችግር ለመፍታት ሊጉ እየሰራ እንደሚገኝና ዘላቂ የሆነ ሰላም ለማረጋገጥ ከህብረቱ ጋር ተቀራርቦ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በሰሜን አፍሪካ አገሮች የሰላምና ጸጥታ ሁኔታ እየሰሩ እንደሚገኙም አብራርተዋል።

በ2020 የጦር መሳሪያ ድምጽ የማይሰማባትን አፍሪካ ዕውን ለማድረግ የተያዘውን እርምጃ ለመደገፍ ሊጉ እንደሚሰራና በሳህል አካባቢ በትብብር የሚሰሯቸው ስራዎች እንዳሉም ጠቁመዋል።

ፕሬዝዳንት መሐሙድ አባስና የአረብ ሊግ ዋና ጸሀፊ አህመድ አቡል-ጌት የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ የ2019 የህብረቱ ሊቀ-መንበር በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም