በንድፈሃሳብና በተግባር ልምምድ ያገኘነው እውቀት ለስራ ፈጠራ መንገድ ይቀይስልናል…ሰልጣኞች

62
ግንቦት 20/2010 በንድፈሃሳብና በተግባር ልምምድ ያገኙት እውቀት ለስራ ፈጠራ መንገድ ይቀይስልናል ሲሉ ኢዚአ ያነጋገራቸው በተለያዩ ኢዱስትሪዎች ስልጠና ላይ የሚገኙ ወጣቶች ተናገሩ፡፡ የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ በበኩሉ የስራ ገበያን መሰረት ያደረጉ ስልጠናዎች ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን አስታውቋል፡፡ በምስራቅ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የሶስተኛ ዓመት ተማሪዋ ፋጡማ ሰይድ የተግባር ላይ ስልጠናውን ከሚከታተሉ ተማሪዎች መካከል አንዷ ናት፡፡ በትምህርት ቆይታዋ የዲዛይንና የስፌት ስራ በልምድ ከሚሰራው የተለየ ጥበብ እንደሚጠይቅ በመገንዘብ እውቀት ማግኘቷን አስረድታለች፡፡ ዘርፉ ለስራ እድል ፈጠራም በቀላል ካፒታል መስራት እንደሚቻል መረዳቷን ነው ያብራራችው፡፡ በኮሌጁ የሚሰጣቸው የልብስ ስፌትና ዲዛይን ስልጠናዎች  እንዲሁም በኢንዱስትሪዎች የሚያደርጉት የተግባር ልምምድ በሞያቸው ብቁ ሆነው እንዲወጡ እገዛ እያደረገላቸው መሆኑን ሌላዋ የኮሌጁ ተማሪ ናርዶስ ጸጋዬ ገልጻለች፡፡ በሌላ በኩሉ በትብብር ስልጠና ቆይታቸው የልብስ ስፌትና ሌሎች ማስተማሪያ ግብአት እጥረት መኖሩ ሁሉም ተማሪዎች በብቃት ልምምድ እንዳያደርጉ እንከን በመፍጠሩ ትኩረት እንደሚያሻው ተማሪዋ ሳትገልጽ አላለፈችም ፡፡ በኮሌጅ ቆይታቸው በንድፈ ሃሳብ ያገኙትን እውቀት በኢንደስትሪዎች የተግባር ላይ ልምምድ  ማድረጋቸው የስራ ባህልን  ለመልመድና የተወዳዳሪነትን ምንጭ በመረዳት የራሳቸውን ስራ ለመፍጠር እንደሚያግዛቸውም ሰልጣኞቹ ተናግረዋል፡፡ ወይዘሮ አበበች ባህሩ በሰብሮም የጋርመንት ኢንደስትሪ የምርት ጥራት ቁጥጥር አስተባባሪ ናቸው ፤ከአስራሦስት ዓመት በፊት በጋርመንት ቴክኖሎጅ ተመርቀው ወደ ስራ ሲገቡ የተግባር ልምምድ የሚያደርጉበት እድል ባለመኖሩ ከቴክኖሎጀው ጋር ለመለማመድ ጊዜ እንደወሰደባቸውና መደናገጥ ፈጥሮባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ ፡፡ አሁን ላይ ተማሪዎች በንድፈሀሳብ የቀሰሙትን እውቀት በተግባር መለማመዳቸው ትልቅ አቅም እየፈጠረላቸው እንደሆነ ማስተዋላቸውን ተናግረዋል፡፡ በመንግስትና በግል ተቋማት የሚሰጡ የስራ ገበያን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ አጫጭርና መደበኛ ስልጠናዎች የምዘና መጠነ ማለፍን ከፍ እያደረገው እንደሆነ የተናገሩት ደግሞ የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ የሰልጣኞች ልማት ዋና የስራ ሂደት ሱፐርቫይዘር አቶ አምባቸው ግርማዬ ናቸው፡፡ በዚህም በ2009 ዓ.ም 83 በመቶ የነበረው የምዘና መጠነ ማለፍ በ2010 86 በመቶ መድረሱን አስረድተዋል፡፡ በመካከለኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት በሚደረገው ጥረት በግልና በመንግስት ኮሌጆችና ተቋማት በ2010 በጀት ዓመት 36ሺ212 ሰልጣኞች የንድፈሃሳብና የተግባር ስልጠናዎች እየወሰዱ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ ሰልጣኞች በንድፈ ሀሳብ ያገኙትን እውቀት በተግባር ማዳበር የሚያስችል የትብብር ስልጠናዎች በ2ሺ 542 ኢንተርፕራይዞችና ኢንደስትሪዎች እየተሰጠ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ የትብብር ሰልጣኞችን በመቀበል በተቋማት ላይ የሚስተዋለውን የተነሳሽነት ችግር ለመቀነስ የተሻለ አፈጻጸም ላሳዩ 200 ተቋማት የእውቅና ሰርተፊኬት መሰጠቱንም አቶ አምባቸው አስረድተዋል፡፡ ተማሪዎቹን የሞያ ባለቤት ከማድረግ ባለፈ ለማደራጀትና ከስራ ጋር እንዲተሳሰሩ ለማስቻል ስልጠናቸውን ያጠናቀቁና የሚሸጋገሩ ወጣቶች 562 ሺ 278 ብር እንዲቆጥቡ መደረጉን ተናግረዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም