ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሰላምና ፀጥታ እንዲረጋገጥ እያደረገችው ያለው እንቅስቃሴ የሚደነቅ ነው - የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀኃፊ

124

አዲስ አበባ  የካቲት 3/2011 ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሰላምና ፀጥታ እንዲረጋገጥ እያደረገችው ያለው እንቅስቃሴ የሚደነቅና ድጋፍ የሚቸረው ነው ሲሉ የመንግስታቱ ድርጅት (የተመድ) ዋና ፀኃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ተናገሩ።

በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ የሚገኙት የተመድ ዋና ፀኃፊ ጉተሬዝ ዛሬ ከቀትር በኋላ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ጋር ተወያይተዋል።

ከውይይቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ በጎረቤት አገራት በተለይም በሶማሊያና ደቡበ ሱዳን ያለውን አለመረጋጋት ተከትሎ በዜጎች ላይ አየደረሰ ያለው እንግልት እንዲቆም እያደረገችው ያለው ውጤታማ የሰላም ጥረት የሚበረታታ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ከጎረቤት ኤርትራ ጋር የነበራትን አለመግባባት በራሷ መንገድ ለመፍታት የወሰደችው እርምጃና የተገኘው አዎንታዊ ውጤትም በመንግስታቱ ድርጅት እንደሚያደንቅ ዋና ፀኃፊው ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የተጀመረው የፖለቲካና ምጣኔ ኃብታዊ የለውጥ ሂደት ግቡን እንዲመታ የመንግስታቱ ድርጅት የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግም አክለዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልማትን ጨምሮ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያካሄዳቸውን የትብብር ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጉተሬዝ አስታውቀዋል።

የተመድ ዋና ፀኃፊ ዛሬ በተጀመረው ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ሰላምና ፀጥታ እንደዚሁም የአየር ለውጥ መዛባት የአፍሪካ አህጉር የወቅቱ ፈተናዎች መሆናቸውን ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ በተመሳሳይ የፍልስጤሙን መሪ መሐመድ አባስን ተቀብለው አነጋገረዋል።

መሐመድ አባሰ አዲስ አበባ የመጡት በአፍሪካ ህብረት 32ኛው የመሪዎቸ ጉባኤ ላይ ለመገኘት ነው።

"አስተማማኝ መፍትሄ በአስገዳጅ ሁኔታ ለሚፈናቀሉ አፍሪካዊያን ስደተኞችና ከስደት ተመላሾች" በሚል መሪ ሃሳብ  እየተካሄደ የሚገኘውና 55 የህብረቱ አባል አገራት መሪዎችን ያሳተፈው ጉባኤው የህብረቱን አሰራር ለማሻሻል በሚካሄደው የለውጥ እርምጃ፣ አህጉራዊ ነፃ የንግድ  ቀጠናውን ወደተግባር መለወጥ የሚቻልበትን መንገድ ጨምሮ በተለያዩ አንገብጋቢ የአህጉሪቱ አጀንዳዎች ላይ ለሁለት ቀን ይመክራል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም