ቻይና የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚን አቅም ለማጠናከር ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆኗን ገለፀች

120
አዲስ አበባ ግንቦት 20/2010 የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ የሚሰጠውን የክህሎትና የምርምር ስራዎች ስልጠና ጠንካራና ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል የአቅም ግንባታ ድጋፍ ለማቅረብ ቻይና ዝግጁ መሆኗን አስታወቀች። ከቻይና የአመራር አካዳሚ የተወጣጣና አስር ፕሮፌሰሮችን የያዘ ልዑካን ቡድን 200 ለሚሆኑ የመለስ አካዳሚ አመራሮችና የምርምርና ጥናት ሙያተኞች የተዘጋጀ የአምስት ቀናት ስልጠና ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል። በዚሁ ወቅት በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ የኢኮኖሚና የንግድ አማካሪ ሚሲስ ሊዩ ዩ እንደገለጹት፤ ቻይና የሁለቱን አገሮች ንግድና ኢንቨስትመንት ከማጠናከር ባሻገር በሰው ኃይል ግንባታና የአመራር ክህሎት ዘርፍ ያላትን ልምድና እውቀት ለማጋራት እየሰራች ነው። በአመራር ክህሎት ልምድ የማካፈል ተግባሩ በጅምር ደረጃ ያለ መሆኑን የገለጹት አማካሪዋ ቀጣይነትና ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማስቀጠል እንዲቻል የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ተመራማሪዎችንና አመራርን በመደበኛ ትምህርትና አጫጭር ስልጠናዎች በማሰልጠን ተቋሙን ለማጠናከርና ለመደገፍ በጋራ ለመስራት ያለውን ዝግጁነት ገልጸዋል። የፌዴራል መለስ የአመራር አካዳሚ ፕሬዚዳንት አቶ አለምነው መኮንን በበኩላቸው የተቋሙን የአቅም ግንባታ ለማጠናከር በቻይና በኩል በተገባው ቃል መሰረት ሁለቱ ወገኖች በጉዳዩ ዝርዝር ሁኔታዎች ላይ እየመከሩ መሆኑን ጠቁመዋል። "ከቻይና ግዙፍ የኢኮኖሚ ዕድገት በስተጀርባ ያለውን የአመራር ክህሎት ውጤታማነትና የህዝብ አገልጋይነት መንፈስ ያለውን ተሞክሮ በስፋትና በጥልቀት ለመማር ከእነሱ ጋር አብረን እንሰራለን፤" ሲሉ ነው አቶ አለምነው የተናገሩት። ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ የቻለችው የቻይና የልማት ፖሊሲና ስትራቴጂን ከራሷ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ስራ ላይ በማዋሏ ጭምር እንደሆነ አቶ አለምነው ተናግረዋል። ቻይናና ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኝነት የተመሰረተው በ1970 ዓ.ም ሲሆን በተለይ በአሁኑ ወቅት በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የኢኮኖሚ ትብብር  ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። ካለፉት ጥቂት ዓመታት ጀምሮ በኢትዮጵያ በእጅጉ እየተስፋፋ በመጣው የመሰረተ ልማት ግንባታ የቻይና ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ በአገሪቱ ውጤታማ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተግባራዊ ይሆኑ ዘንድ የሚያስፈልጉ ጥናትና ምርምሮችን ያካሂዳል፤ ተያያዥ የሆኑ ስልጠናዎችንም ለመንግስት የስራ ኃላፊዎች ይሰጣል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም