የጎንደር ነዋሪዎች መንግሥት ሰላማቸውን በሚያደፈርሱ ኃይሎች ላይ እርምጃ እንዲወስድ ጠየቁ

73

ጎንደር  የካቲት 3/2011 መንግሥት የአማራና የቅማንት ሕዝቦችን ወደ ግጭት በማስገባት የአካባቢውን ሰላም ለማደፍረስ በሚጥሩ ኃይሎች ላይ  እርምጃ እንዲወስድ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡

የጎንደር የሰላምና የልማት ሸንጎ ከጎንደር የአማራ ወጣቶች ማህበር ጋር በመተባበር የከተማውን ሰላም ላይ ያተኮረ ሕዝባዊ ውይይት ትናንት አካሂደዋል፡፡

ነዋሪዎቹ አካባቢውን ወደ ግጭት ቀጠና ለመለወጥ የሚጥሩ የታጠቁ ኃይሎች ድርጊት ለመግታት መንግሥት እርምጃ ሊወስድ ይገባዋል ብለዋል።

በምዕራብ ጎንደር የተጀመረው ግጭት በከተማው ሰላም ስጋት ደቅኗል ያሉት ተሳታፊዎቹ፣ መንግሥት ለችግሩ አፋጣኝ እልባት እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

በታጣቂ ኃይሎቹ  እየደረሰ ያለውን የንጹሃን ወገኖች ሞት፣ መፈናቀልና የንብረት ውድመትም አውግዘዋል፡፡

ወይዘሮ የሺ ማሩ የተባሉ ነዋሪ በሰጡት አስተያየት በጋራ አብሮ የመኖር እሴት የገነቡትን ሁለቱን ሕዝቦች ለማጋጨትና ለማለያየት ሕገ-ወጥ ቡድኖች የሚሸርቡት ሴራ የአካባቢውን ሰላም እያደፈረሰው ነው ብለዋል፡፡

ለውጥ አደናቃፊ ኃይሎች አካባቢውን የጦርነት ቀጠና እንዲሆን የሚያደርጉት ጥረት መንግሥት በአፋጣኝ ሊገታው ይገባል ያሉት ደግሞ አቶ ታረቀኝ ሙሉአለም የተባሉ ነዋሪ ናቸው፡፡

በጎንደር የአማራ ወጣቶች ማህበር አስተባባሪ ወጣት ይሁኔ ዳኘው የከተማውን ማህበሩ በየደረጃው በፈጠራቸው አደረጃጀቶች ከጸጥታ ኃይሉ ጋር ተቀናጅቶ ሰላምን ለማስጠበቅ እየሰራ መሆኑን ተናግሯል፡፡

የከተማው የሰላምና የልማት ሸንጎ ሰብሳቢ አቶ ባዩ በዛብህ በበኩላቸው ሁለቱን ሕዝቦች ለማጋጨት የሚፈልጉ ኃይሎችን እኩይ ተግባር በማጋለጥ ለከተማው ሰላምና ልማት በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የጎንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ሙሉቀን አዳነ የሰላሙ ባለቤት ሕዝቡ እንደመሆኑ ግጭትና ብጥብጥ ለመፍጠር የሚሯሯጡ ሕገ-ወጦችን ሊታገላቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

መንግሥት የብጥብጥና የሁከት አጀንዳ በመንደፍ በሕዝቦቹ መካከል ግጭት የሚፈጥሩ ኃይሎች ላይ  እየወሰደ ያለውን እርምጃ   ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ነዋሪዎቹ የከተማውን ሰላም በአስተማማኝ ለመጠበቅና ግጭት ፈጣሪዎችን ለሕግ ለማቅረብ ተስማምተዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ከሶስት ሺህ በላይ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም