ታይላንድ የሙይታይ ስፖርትን በኢትዮጵያ ለማስፋፋት እንቅስቃሴ ጀምራለች

58

አዲስ አበባ የካቲት 2/2011 ታይላንድ የምትታወቅበትንና ከነጻ ትግል ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ጋር ተመሳሳይነት ያለውን 'ሙይታይ' የተሰኘ ስፖርት በኢትዮጵያ ለማስፋፋት እንቅስቃሴ ጀምራለች።

የሙይታይ ስፖርትን የሚያስተዋዉቁ የታይላንድ ልኡካን ቡድን አባላት ዛሬ በአራት ኪሎ ስፖርት ትምህርትና ስልጠና ማዕከል ለኢትዮጵያውያን ስፖርተኞች በዘርፉ የተግባር ስልጠና ሰጥተዋል።

የታይላንድ የቦክስ ስፖርት እየተባለ የሚጠራው 'ሙይታይ'  በአገሪቱ የተጀመረው በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ነው።

ከ300 ዓመት በላይ እድሜ ያስቆጠረው ስፖርታዊ ውድድሩ ቡጢ፣ ክርን፣ ቅልጥምና ጉልበትን በመጠቀም የሚካሄድ መሆኑ ከሌሎች የነጻ ፍልሚያ ውድድሮች ለየት እንደሚያደርገው ይነገርለታል።

የታይላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመረጃ የስራ ክፍል የባህል ዲፕሎማሲ ዘርፍ ምክትል ሃላፊ አታይካርን ኮንዋይ ለኢዜአ እንደገለጹት ስፖርቱ በኢትዮጵያ ባሉ የተወሰኑ የሙይታይ ስፖርት ክለቦች እየተዘወተረ ነው።

ታይላንድ ስፖርቱን በመላው ዓለም የማስተዋወቅ ተግባር እያከናወነች መሆኑንና ኢትዮጵያ የዚሁ አካል እንደሆነች ተናግረዋል።

"የኢትዮጵያ ህዝብ ስፖርት ወዳድ ነው ስፖርቱን ለማስተዋወቅ ወደዚህ ስንመጣ ጥሩ ነገር እንደሚጠብቀን ገምተን ነበር ያገኘነው ይህንኑ ነው" ብለዋል።

ታይላንድ በተወሰነ መጠን በኢትዮጵያ የሚዘወተረውን የሙይታይ ስፖርት ለማስፋፋት እና በአጠቃላይ በስፖርቱ መስክ ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ ትብብር የመፍጠር ፍላጎት እንዳላትም አንስተዋል።

በቀጣይም የስፖርቱ ተወዳዳሪዎች በታይላንድ ስልጠና እንዲያገኙና ልምድ እንዲቀስሙ እቅድ መኖሩንም ጠቅሰዋል። ቡድኑ በድጋሚ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣልም ብለዋል።

የሙይታይ ስፖርት በኢትዮጵያ እንዲስፋፋ መደረጉ በህዝቦች መካከል የባህልና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንዲያድግ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ጠቅሰዋል።

የአዲስ አበባ ኢንተግሬትድ ማርሻል አርት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን ሃይሉ በበኩላቸው የስፖርት ትውውቁ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ስፖርቱን ይበልጥ እንዲዘወተርና እድገት እንዲኖረው ምቹ አጋጣሚ ይፈጥራል ብለዋል።

የልዑካን ቡድኑ አባላት ከጥር 27 እስከ 29 ቀን 2011 ዓ.ም ስፖርቱን የማስተዋወቅ ስራ በኬንያ ያከናወኑ ሲሆን እስከ የካቲት 17 ቀን 2011 ዓ.ም ባለው ጊዜ አባላቱ በሞዛምቢክና በደቡብ አፍሪካ የማስተዋወቅ ስራ እንደሚያከናውኑም ለማወቅ ተችሏል።

የሙይታይ ስፖርት እ.አ.አ በ2016 በዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ እውቅና አግኝቶ የአሎምፒክ ስፖርት የሆነ ሲሆን እ.አ.አ በ2024 በፓሪስ በሚካሄደው 33ኛው የአሎምፒክ ውድድር ላይ ለማካተት ጥረት እየተደረገ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም