የፕሪሚየር ሊጉ 15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከነገ ጀምሮ ይካሄዳሉ

67

አዲስ አበባ የካቲት 2/2011 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከነገ ጀምሮ ይካሄዳሉ።

ነገ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰዓት መከላከያ ከኢትዮጵያ ቡና ይጫወታሉ።

በክልል ከተሞችም ነገ ሶስት ጨዋታዎች ሊካሄዱ መርሃ ግብር ተይዞላቸዋል።

በወላይታ ሶዶ ስታዲየም ወላይታ ድቻ ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ባህርዳር ከተማ ከአዳማ ከተማና በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ደደቢት ከሀዋሳ ከተማ በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ይጫወታሉ።

ከነገ በስቲያ ደግሞ ፋሲል ከተማ ከስሑል ሽረ፣ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ ከሲዳማ ቡና እና ደቡብ ፖሊስ ከጅማ አባጅፋር ጋር በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ጨዋታቸውን ይጀምራሉ።

የወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲና የሲዳማ ቡና ጨዋታ ዛሬ መደረግ የነበረበት ቢሆንም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጨዋታው የሚካሄድበትን ቀን መቀየር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ሰኞ የካቲት 4  ቀን 2011 ዓ.ም እንዲደረግ መወሰኑ የሚታወስ ነው።

ማክሰኞ የካቲት 5 ቀን 2011 ዓ.ም ድሬዳዋ ከተማ ከመቐለ ሰብዓ እንደርታ ጋር ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የ15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ጨዋታዎች ቢሆኑም በተለያዩ ምክንያቶች የተራዘሙ ስምንት ተስተካካይ ጨዋታዎች በመኖራቸው ውድድሩ እስከ የካቲት 21 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ እንደሚቆይ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣መቐለ ሰብዓ እንደርታና ሲዳማ ቡና በተመሳሳይ 26 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ሲይዙ ኢትዮጵያ ቡና በ22 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ላይ ተቀምጧል።

ስሑል ሽረ፣ደቡብ ፖሊስና ደደቢት በቅደም ተከተል ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

የፕሪሚየር ሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የመከላከያው ምንይሉ ወንድሙ በ11 ግቦች ሲመራ፣የመቐለው አማኑኤል ገብረሚካኤልና የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ በተመሳሳይ ዘጠኝ ግቦች ይከተላሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም