የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ

126

አዲስ አበባ የካቲት 2/2011 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖምን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ።

የውይይቱ ትኩረት  በጤናው ዘርፍ ላይ በተለይም ድንበር ዘለል በሽታዎችን መከላከል ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኃላፊነትንና ዝግጁነትን እንደዚሁም ከሌሎች አገራት ጋር  በጋራ መስራት ስለሚኖርባቸው ጉዳዮች ነው።

ዶክተር ቴድሮስ ከውይይቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት ድንበር ዘለል በሽታዎችን ለመከላከል የአገራትን በሽታ የመከላከል፣ በሽታዎችን በፍጥነት የመለየትና በቁጥጥር ስር የማዋል አቅም መገንባት ዋናው መፍትሄ ነው።

ለዚህም የዓለም የጤና ድርጅት ድንበር ዘለል በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስችሉና አገራት በጋራ የሚተገብሯቸው የተለያዩ መመሪያዎች ማዘጋጀቱንም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ድንበር ዘለል በሽታዎችን መከላከል ላይ በጋራ ለመስራት ዝግጁነት መኖሩን በውይይቱ መገንዘባቸውን ዶክተር ቴድሮስ ገልፀዋል። 

ዶክተር ቴድሮስ እንደተናገሩት ድንበር ዘለል ተላላፊ በሽታዎች መከላከል ላይ የአገራትን ዝግጁነት በተመለከተ በተደረገ ጥናት ኢትዮጵያ መካከለኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

የዓለም የጤና ድርጅት ድንበር ዘለል በሽታዎችን መከላከል ላይ ያሉ ክፍተቶችን በመለየት የመከላከሉን ስራ ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል። 

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የእናቶችና የህጻናትን ሞት በመቀነሱና የጤና ሁኔታዎችን በማሻሻል  በኩል ለውጦች ቢኖሩም አሁንም ችግሮች መኖራቸውን የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የመሰረታዊ የጤና አገልግሎትን በማጠናከር የእናቶችንና የህጻናትን የጤና አገልግሎት ለማሻሻል በጤና ሚንስቴር በኩል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚደግፍም ተናግረዋል። 

በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት ለማድረግ አዲስ አበባ የሚገኙት ኢትዮጵያዊው ዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ ትናንት ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋርም በአገሪቱና በድርጅቱ መካከል በትብብር በሚካሄዱ የጤና ልማት ዘርፎች ላይ መክረዋል።

ኢትዮጵያ የመሰረታዊ ጤና አገልግሎትን ለማሳካት የምታደርገውን ጥረት የዓለም ጤና ድርጅት ድጋፍ መስጠቱን እንደሚቀጥል የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ለፕሬዚዳንቷ አረጋግጠዋል።

የጤና አገልግሎቱን ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ እንዲሆን በተለይም ከወረዳ ጀምሮ የሚደረገው እንቅስቃሴ ከፍተኛ አድናቆት የሚቸረው ነው፤ ይህንን የኢትዮጵያን ተሞክሮ እንደ ጥሩ ምሳሌ በመውሰድ በሌሎች ሀገራትም ለማስፋፋት እንደሚሰሩ ዶክተር ቴድሮስ ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም