ሰራዊቱ ሰላምን የማስጠበቅ ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥላል---በመከላከያ ሰራዊት የምስራቅ እዝ አዛዥ

90

ሀረር የካቲት 2/2011 የመከላከያ ሰራዊት ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ለውጥ እያሳየ የሚገኘውን ሰላም የማረጋገጥ ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል ዘውዱ በላይ ገለጹ።

በሀረሪ ክልል 7ኛውን የመከላከያ ቀን በማስመልከት የዕዙ አባላት በልማትና በበጎ አድራጎት ስራዎች ሲያከብሩትበት የነበረው ዝግጅት ተጠናቋል።

በሀረር ከተማ ጨለንቆ ሰማዕታት መሰብሰቢያ አዳራሽ በተከናወነ የማጠናቀቂያ ስነ-ስርዓት ላይ አዛዡ እንዳሉት የሰራዊቱ አባላት ከክልሉና ከአጎራባች ከተሞች ነዋሪዎች ጋር በአንድ ዓላማ በመሰለፍ የልማትና የሰላም ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

በተለይ በክልሉ ይታዩ የነበሩ የሰላም፣የልማት፣የመልካም አስተዳደርና ሌሎች ችግሮች ከአመራሩና ከህብረተሰቡ ጋር በመወያየት እየተቃለሉ በመሆናቸው የተሻለ ሰላም መስፈኑንና ለዚህም የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበረ ተናግረዋል።

“ሰራዊቱም የለውጥ አካል እንደመሆኑና በሪፎርም ውስጥ እንደመገኘቱ አገርና ህዝብ የጣለበትን ትልቅ አደራ  በብቃት ለመወጣት የሰላም ሃይል ሆኖ ይቀጥላል” ሲሉ ተናግረዋል።

የክልሉ ነዋሪዎች በተለያዩ መንገዶች የህብረተሰቡን ሰላም ለማወክና ግጭት ለመፍጠር የሚጥሩ ሀይሎችን መታገልና መከለከል እንደሚገባ ገልጸው ሰራዊቱም ከህዝቡ ጋር  የጀመረውን ሰላምን የማረጋገጥ ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በክልሉ አንድ አንድ የመልካም አስተዳደር ችግሮች አለመፈታታቸው፣ ህዝባዊ መድረክ በማዘጋጀት የህዝብ ጥያቄን ለመፍታት የሚከናወኑ የውይይት እንቅሰቃሴዎች መዳከማቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ የሪፎርም ስራዎች አለመጠናከር፣ከለውጡ ጋር የሚሄድ አመራር አለመሾም፤ ኪራይ ሰብሳቢና ኮንትሮባንዲስቶችን ለህግ የማቅረብ ስራ ላይ የሚታይ ክፍተት መፍትሔ የሚሻ ጉዳይ መሆኑንም ገልጸዋል።

በውይይቱ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ “ህዝቡ የሚያነሳውን ጥያቄ ለመመለስና በክልሉ እየታየ የሚገኘውን አንጻራዊ ሰላም ለማጠናከር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የክልሉ መንግስት እየሰራ ነው” ብለዋል።

ህብረተሰቡን ለማወያየት መድረኮች በሚፈለገው ደረጃ እየተዘጋጁ አለመሆናቸውን ጠቅሰው በቀጣይ ከወጣቶችና ሴቶች፣ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሀይማኖት አባቶችና ከነዋሪዎች ጋር መድረክ በማዘጋት ችግሮችን የማቃለል ስራ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

“የልማት፣የመልካም አስተዳደርና ሌሎች ስራዎች መከናወን የሚችሉት ሰላም ሲሰፍን ነው” ያሉት ርዕሰ-መስተዳድሩ “ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን በመቆም የጀመረውን ሰላምን የማረጋገጥ ስራ ማጠናከር ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።

በመዝጊያው ስነ ስርዓት የክልሉና የምስራቅ ዕዝ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣የሀገር ሽማግሌና የሐይማኖት አባቶች፣አባገዳዎች ወጣቶች ተገኝተዋል።

ለ15 ቀናት በክልሉ በተከበረው 7ኛው የመከላከያ ሰራዊት ቀን በዓል ሰራዊቱ 75 ዩኒት ደም ከመለገስ ባለፈ፤ በከተማው ለሚገኘው ሐረር የሀገር ልጅ በጎ አድራጎት ማህበር የ50 ሺ ብር ድጋፍ እንዲሁም የጽዳት ዘመቻና ሌሎች የልማትና የበጎ አድራጎት ስራ አከናውኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም