የእምቦጭ አረም ስጋትን ለማስወገድ ሀገር አቀፍ ትኩረት ተሰጥቷል....የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን

59

ጎንደር የካቲት 2/2011 በሀገሪቱ የተለያዩ የውሃ አካላት ላይ የተጋረጠውን የእምቦጭ አረም ስጋት ለማስወገድ ሀገር አቀፍ ትኩረት መሰጠቱን የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ 

የኢትዮጵያ አሣና ውሃ ሳይንስ ባለሙያዎች ማህበር 11ኛው ዓመታዊ ኮንፍረንስ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በመካሄድ ላይ ነው፡፡

በኮንፍረንሱ ላይ የተገኙት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ እንደተናገሩት ጣና ሐይቅን ጨምሮ በተለያዩ የውሃ አካላት ህልውና ላይ ስጋት የደቀነውን የእምቦጭ አረም ለማስወገድ መንግስት የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅዶችን ነድፎ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡

ከአጭር ጊዜ አኳያ በቂ በጀትና ቁሳቁስ በመመደብ አረሙን በሰው ኃይልና በማሽነሪ ታግዞ ለማስወገድ የተጀመረው እንቅስቃሴ ስኬታማ እንዲሆን መንግስት የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

"ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከምርምር ማዕከላት ጋር የቅርብ ግንኙነት በመመስረትም አረሙን በሳይንሳዊ መንገድ ለማስወገድ የሚያስችሉ ጥናትና ምርምሮች እንዲከናወኑ እየተደረገ ነው" ብለዋል፡፡ 

ኮሚሽኑ ንጹህ የመኖሪያ አካባቢ እንዲኖር፣ የውሃ ብክለትን የመቆጣጠር፣ ብዝሃ ህይወትን የመጠበቅ፣ የደን ልማትን በማስፋፋት የአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣውን ተጽእኖ የመቀነስ ስራዎችን እያስተባበረ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አሣና ውሃ ሳይንስ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ታደሰ ፈታሂ በበኩላቸው "በካይ ንጥረ ነገሮች ወደ ውሃ አካላት በብዛት በመግባት የእምቦጭ አረም እንዲስፋፋ እያደረጉ ናቸው" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በማህበሩ 11ኛው ዓመታዊ ኮንፍረንስ ላይም በካይ ንጥረ ነገሮች ዋነኛ የውሃ አካላት የችግር ምንጮች መሆናቸውን የሚያመላክቱ ጥናታዊ ጽሁፎች በጥናት አቅራቢዎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው አስረድተዋል።

ዶክተር ታደሰ እንዳሉት የእንቦጭ አረምን ለማስወገድ እየተደረገ ያለውን የተናጥል ጥረት በተደራጀ አግባብ መምራት እንዲቻልም ማህበሩ ከፌደራልና ከክልል ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ ነው፡፡

የእምቦጭ አረም ሀገር አቀፍ ጉዳይ ሆኖ ትኩረት እንዲያገኝ ለማድረግም ማህበሩ ኮሚቴ አቋቁሞ በመጪው ሰኔ ሀገር አቀፍ ጉባኤ ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጀመሩንም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ደሳለኝ መንገሻ በበኩላቸው በጣና ሐይቅ ላይ የተስፋፋውን የእምቦጭ አረም ለመግታት ዩኒቨርሲቲው አንድ የእምቦጭ አረም ማስወገጃ ማሽን ሰርቶ ለሙከራ ማብቃቱን ገልጻዋል፡፡

" በምርምር ዘርፍምየሐይቁን ብዝሃ ሕይወት በማይጎዳ ሁኔታ አረሙን በሳይንሳዊ መንገድ ማስወገድ እንዲቻል በመምህራን የጥናትና ምርምር ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው" ብለዋል፡፡

ዛሬ ይጠናቀቃል ተብሎ በሚጠበቀው ኮንፍረንስ ላይ የውሃ አካላትን ብክለት ለመቀነስ በሚያስችሉና የአምቦጭ አረም መስፋፋትን ሊገቱ በሚችሉ ሳይንሳዊ ጥናቶች ላይ ያተኮሩ 27 ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ነው፡፡

የዛሬ 10 ዓመት የተቋቋመው የኢትዮጵያ አሣና ውሃ ሳይንስ ባለሙያዎች ማህበር በአሁኑ ወቅት የአባላቱ ቁጥር 400 መድረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም