በቦሌ ክፍለ ከተማ የአማራ ክልል ተወላጆች ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አደረጉ

78

ባህር ዳር የካቲት 2/2011 በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ የሚኖሩ የአማራ ክልል ተወላጆችና የአዴፓ አባላት  ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች  የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ።

ግምቱ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚሆን የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ ለክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ትናንት አስረክበዋል።

በርክክቡ ወቅት በቦሌ ክፍለ ከተማ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ውቤ ነጋሽ እንደተናገሩት ሰው ሰራሽ በሆኑ ችግሮች ምክንያት ዜጎች ከቤት ንብረታቸው እየተፈናቀሉ ነው።

በአማራ ክልልና ከክልሉ ውጭ በርካታ የክልሉ ተወላጆች መፈናቀላቸውን አስታውሰው ለተፈናቃዮች ከጎናቸው መሆናቸውን ለማሳየት ከነዋሪዎች የተሰባሰበውን እርዳታ ይዘው መምጣታቸውን አመልክተዋል።

በእርዳታውም ከ700 ኩንታል በላይ ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ሩዝ፣ ፍርኖ ዱቄትና ማካሮኒ በተጨማሪ 1 ሺህ 357 ሊትር ዘይትና ሌሎች የምግብ እህሎችን ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በድጋፉ 373 ፍራሽና ብርድ ልብስ፣ የተለያዩ የግል ንጽህና መጠበቂያና ሌሎች ተጨማሪ ቁሳቁሶች እንደሚገኙበት አቶ ውቤ አስረድተዋል።

በዜጎች ላይ እየደረሰ ባለው መፈናቀል ህፃናትና ሴቶች በቀዳሚነት የችግሩ ሰለባ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በክፍለ ከተማው የአማራ ሴቶች ማህበር አስተባባሪ ወይዘሮ አልማዝ በፍቃዱ ናቸው።

የተደረገው ድጋፍ ለችግሩ ተጠቂዎች በትክክል ስለመድረሱ ክትትል እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

ተፈናቃዮቹ ወደተፈናቀሉበት ቀዬ ተመልሰው በዘላቂነት እስኪቋቋሙ ድረስም ነዋሪዎቹ የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የህዝብ ግንኙነት አማካሪ አቶ ደሴ ጥላሁን በበኩላቸው እንዳሉት ከአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ የተውጣጡ አመራሮችና ነዋሪዎች ያደረጉት ወገናዊ ድጋፍ የሚያስመሰግን ነው።

የተደረገውን ድጋፍ የክልሉ መንግስት ለተፈናቀሉ ወገኖች በፍጥነት እንደሚያደርስም አመልክተዋል።

አቶ ደሴ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት ያለውን ሀገራዊ ለውጥ ወደኋላ ለመጎተት ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች የተለያዩ የማደናገሪያ አጀንዳዎችን እያነሱ ህዝቡን ለእንግልትና ጉዳት እየዳረጉት ይገኛሉ።

ድርጊቱ እንዲቆም ህዝቡ በጋራ መስራትና ፖለቲካዊ መፍትሄ ማስቀመጥ አስፈላጊ ገልጸው፣ "ህብረተሰቡ ለተፈናቃዮች እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል" ብለዋል።

የቦሌ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ለተፈናቀሉ ወገኖች ያደረጉት ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማተባበሪያ ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ እያሱ መስፍን ናቸው።

በቅርቡም የቂርቆስና የአዲስ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ከ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን ቁሳቁስ ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎችና በክልሉ ውስጥ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ከ60 ሺህ በላይ ሰዎች በክልሉ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም