ታይላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ማሳደግ ትፈልጋለች

80

አዲስ አበባ የካቲት 2/2011  ታይላንድ ከኢትዮጵያ ጋር በንግድና ኢንቨስትመንት መስኮች ያላትን ትብብር ማሳደግ እንደምትሻ በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር ቼርዲያት አታኮር ገለፁ።

'ሙይታይ' የተሰኘውን የታይላንድ ስፖርት የሚያስተዋዉቁ የቡድን አባላት ዛሬ ለኢትዮጵያውያን ስፖርተኞች የተግባር ስልጠና ሰጥተዋል።

በዚሁ ወቅት የኢዜአ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አምባሳደር ቼርዲያት አታኮርን ኢትዮጵያና ታይላንድ በጋራ ተጠቃሚነትና መግባባት ላይ የተመሰረተ መልካም ግንኙነት እንዳላቸው ነው የገለፁት።

ያም ቢሆን አገራቱ በንግድና ኢንቨስትመንት ያላቸው ግንኙነት ዝቅተኛ መሆኑን አንስተዋል።

እርሳቸው እንዳሉት በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የሁለቱ አገራት የንግድ ልውውጥ መጠን ከ50 ሚሊዮን ዶላር አይበልጥም።

የታይላንድ መንግስት ይህ የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነቱ በሚፈለገው መጠን እንዲያድግ ፍላጎት እንዳለውም አክለዋል።

ባለፈው መስከረም ወር 2011 ዓ.ም በምግብ ኢንዱስትሪ፣ በተሽከርካሪ መገጣጠሚያና በግንባታ ዘርፍ የሚገኙ ከ35 በላይ የታይላንድ ኩባንያዎች ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል።

በዚሁ ወቅትም ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋር የተወያዩ ሲሆን በአገሪቱ ያሉትን የቢዝነስ አማራጮች ተመልክተዋል።

በተያዘው የፈረንጆች ዓመት ውስጥም ሌሎች የታይላንድ ኩባንያዎች ተጨማሪ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማጥናት  ወደኢትዮጵያ ይመጣሉ፤ ለዚህ ያግዛቸው ዘንድም የቢዝነስ ፎረም ለማዘጋጀት እቅድ መያዙን አምባሳደሩ አክለው ገልፀዋል።

አምባሳደር ቼርዲያት አታኮር እንዳሉት የታይላንድ መንግስት የአገሪቷ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥረት እያደረገ ነው።

የታይላንድ የግብርና ምርቶች ፋብሪካ የሆነው ሲፒ ግሩፕ በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት እንዳለውና በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያ በዘርፉ ያሉትን አማራጮች እየተመለከተ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ላይ እንደምትገኝና በአሁኑ ሰአት በአገሪቱ ያለው የንግድና ኢንቨስትመንት ሁኔታ ምቹ በመሆኑ በዘርፉ ያለውን ግንኙነት ለማሳደግ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር ነው አምባሳደሩ ያስረዱት።

መንግሥት የልማት ድርጅቶችን በከፊል ወደ ግል የማዘዋወር ሂደት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ክፍት እንዲሆን የሚያደርግ በመሆኑ ለታይላንድና ለሌሎች አገራት ኩባንያዎችም መልካም አጋጣሚ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ለውጥ አገሪቱን ወደ ትክክለኛ መንገድ እንደሚመራት የታይላንድ መንግስት እንደሚያምንና ለውጡ መልካም የሚባል እንደሆነ ተናግረዋል።

በተለይም በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ለምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ወሳኝ ሚና እንዳለው ያነሱት አምባሳደሩ ከግጭት ይልቅ ተስማምቶ በሰላምና በአንድንት መኖር እንደሚቻል ለሌሎች ምሳሌ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ሁለቱ አገራት በጤና፣ በልማትና በምግብ ዋስትና መስኮች ጠንካራ የሚባል ትብብር እንዳላቸውና ታይላንድ ከንግድና ኢንቨስትመንቱ በተጨማሪ በአገልግሎት ዘርፉም ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖራት ትፈልጋልች ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስትም ከታይላንድ ጋር ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት የማጠናከር ፍላጎት እንዳለው ከመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ማረጋገጥ እንደቻሉም አንሰተዋል።

ታይላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የምታካሂደው ኬንያ ባለው የአገሪቱ ኤምባሲ እንደሆነና በቀጣይ በኢትዮጵያ ኤምባሲ የመክፈት ጉዳይ እየታሰበበት መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያና ታይላንድ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1960 ነው።

ኢትዮጵያ በታይላንድ ርዕሰ መዲና ባንኮክ የቆንስላ ጽህፈት ቤት ያላት ሲሆን ከታይላንድ ጋር የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን የምታከናውነው ህንድ በሚገኘው ኤምባሲዋ በኩል ነው። 

ኢትዮጵያ ከታይላንድ የመኪና መለዋዋጫ እቃዎች፣ ሩዝና የምግብ ዘይት ስታስገባ የግብርና ምርቶችን ደግሞ ወደዚያ ትልካለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም