በጮቄ ተራራ የሚደርሰውን የተፈጥሮ ሀብት ብክነትን ለመታደግ ህብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ

937

ደብረማርቆስ የካቲት2/2011 በምስራቅ ጎጃም ጮቄ ተራራ ላይ እየደረሰ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ብክነት ለመታደግ ህብረተሰቡ የድርሻውን አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አስገነዘቡ።

በፌደራል ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽንና በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ትብብር የተዘጋጀ የማህበረሰብ ውይይት መድረክ ትላንት ተካሂዷል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በወቅቱ እንደገለጹት በጮቄ ተራራ እየደረሰ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት መመናመን በመታደግ የአካባቢውን ስነ- ምህዳር ጠብቆ ለማቆየት እየተሰራ ነው።

በመንግስትና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ትብብር የተራራውን ተፋሰስ የማልማት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የገለፁት ርዕሰ መስተዳደሩ ህብረተሰቡ በልማቱ በመሳተፍ የድርሻውን አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

በአካባቢው ባለፉት አራት ዓመታት በህብረተሰቡ ተሳትፎ የተከለሉ ጥብቅ ቦታዎችን ለማልማት በተከናወኑ ተግባራት አንጻራዊ ለውጥ መታየቱን አስታውሰው ህብረተሰቡ በዘርፉ ሲያሳየው የነበረው ተሳትፎ በአሁኑ ወቅት እየተዳከመ መምጣቱን ተናግረዋል።

“ማህበረሰቡ በአካባቢ ጥበቃ ሥራ ላይ የነበረውን ተሳትፎ በማጠናከር ለትውልድ የሚተላለፍ ተግባር ሊያከናውን ይገባል” ብለዋል 

ጮቄ ተፋሰስ የአፍሪካ የውሃ ማማ በመሆን የአባይ ግድብን ጨምሮ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገሮች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም አቶ ገዱ ተናግረዋል።

በፌደራል አካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ  የብዝሃህይወት ማትጊያና ማካተቻ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ አብደታ ደበላ  ከፌደራል እስከ ወረዳ ባሉ የአካባቢ ጥበቃ አካላት የሚከናወኑ የተፋሰስ ልማት ስራዎችን የማገዝና የማበረታታት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

በልማት ሥራዎቹ አስፈላጊነት ላይ ከህብረተሰቡ ጋር የጋራ መግባባት ላይ መደረሱንና ተሳትፎውን የማጠናከር ሥራ እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ የውይይት መድረኩም የእዚህ አካል መሆኑን ጠቁመዋል።

በጮቄ ተፋሰስ ልማት ህብረተሰቡን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው ዶሮች፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ዘሮች መቅረባቸውን አስታውሰው ወደፊት አቅርቦቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል ።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የሴዴ እና የደባይ ጥላን ግን ወረዳ ነዋሪዎች ለጮቄ ተራራ ተፈጥሮ ሀብት መመናመን ምክንያቶች አንዱ የመንግስት ቁርጠኝነት ማነስ መሆኑን በመግለጽ ተፋሰሱን ለማልማት በሚደረገው ጥራት ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል። የአካባቢውን ማህበረሰብ ፍላጎት መሰረት በማድረግ ከስድስት ዓመት በፊት በጮቄ ተራራ 6 ሺህ 24 ሄክታር መሬት ለልማት መከለሉ ታውቋል።