በጋምቤላ ክልል የመንግስት መስሪያቤቶች የሥራ ሰዓት ለውጥ ተደረገ

69

ጋምቤላ የካቲት 2/2011 በጋምቤላ ክልል እየጨመረ የመጣውን የሙቀት መጠን ተከትሎ ለሦስት ወራት የሚቆይ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሥራ ሰዓት ለውጥ ተደረገ፡፡

የክልሉ መንግስት መስተዳደር ምክር ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የላከው መግለጫ እንዳመለከተው በአሁኑ ወቅት በክልሉ እየጨመረ የመጣውን የሙቀት መጠን ተከትሎ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የመግቢያና የመውጫ የሥራ ሰዓት በጊዜያዊነት ተለውጧል፡፡

በዚህም ጧት የሥራ መግቢያ 1፡00 ሲሆን መውጫው 5፡30 እንዲሁም ከሰዓት በኋላ የሥራ መግቢያ 10፡00 ሰዓት ሲሆን መውጫው 12፡30 መደረጉ ተመልክቷል።

የሥራ ሰዓት ለውጡ ተግባራዊ የሚሆነው ከየካቲት 1 ቀን 2011 እስከ ሚያዚያ 30 ቀን 2011 ዓ.ም መሆኑን የገለጸው መግለጫ ጋምቤላ ከተማን ጨምሮ በክልሉ ከፍተኛ ሙቀት በሚታይባቸው ቆላማ አካባቢዎች ጭምር ተግባራዊ ይደረጋል፡፡

የሥራ ሰዓት ለውጡ በክልሉ ደጋማ የማጃንግ ብሔረሰብ ዞን የሚገኙ ወረዳዎችን እንደማያካትት ታውቋል፡፡

ከኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ጋምቤላ ቅርንጫፍ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በክልሉ በአሁኑ ወቅት ያለው የሙቀት መጠን ከፍተኛው 42 ዲግሪ ሴልሺየስ ሲሆን ዝቅተኛው 22 ዲግሪ ሴልሺየስ ነው።

ከተያዘው የካቲት ወር ጀምሮ እስከ ሚያዚያ ወር መጨረሻ በጋምቤላ ክልል ከፍተኛ የሙቀት መጠን የሚመዘገብት ሲሆን ዝቅተኛው የሙቀት መጠን በነሃሴ ውር እንደሚመዘገብ ታውቋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም