በአፍሪካ የምርት እድገትንና ብዝሃነትን ማረጋገጥ ቁልፍ ተግባር እንደሆነ ህብረቱ አመለከተ

48

አዲስ አበባ የካቲት 1/2011 የአፍሪካ ህብረት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ኮሚሽን የምርት ዕድገትንና ብዝሃነትን ለማረጋገጥ ትኩረት በመስጠት እንደሚሰራ አመለከተ።

የህብረቱ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ቪክቶር ሃሪሰን ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ በሰጡት መግለጫ ፤ የአፍሪካ አገሮች እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርትን ከውጭ አስገብተው እንደሚጠቀሙ ገልፀዋል። 

ይህንን ችግር ለመፍታት ወሳኙና ቁልፉ ጉዳይ ምርትን ማሳደግና የምርት ብዝሃነትን ማስፋፋት እንደሆነ አስረድተዋል።

የአፍሪካ አገሮች በምርት አቅርቦት ራሳቸውን ባለመቻላቸው የግብርና ምርትን ከውጭ እያስገቡ እንደሆነ የገለጹት ኮሚሽነሩ ''አሁንም በሚሊዮኖች ቶን የሚገመት የሩዝ ምርት ወደአህጉራችን እናስገባለን'' ብለዋል።

ይህንን ችግር ለመፍታት የግብርና ምርትን ለማሳደግ መስራት አስፈላጊና ወሳኝ እንደሆነ ነው ኮሚሽነሩ የጠቆሙት።

አፍሪካ የምርታማነት ማሳደግ ሽግግር እንደሚያስፈልጋት የገለፁት ፕሮፌሰር ሃሪሰን የግብርናና የኢንዱስትሪ ዘርፉን ከአገልግሎት ዘርፍ ጋር አብሮ እንዲራመድ የሚያስችል ተግባር መከናወን እንዳለበትም አሳሰበዋል።

በዚህ ረገድ የተሻለ ለውጥ ለማምጣት የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ መስራት እንደሚያስፈልግ ነው ኮሚሽነሩ የተናገሩት።

የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማቀላጠፍ የሚያስችል የፖሊሲ ዝግጅት በህብረቱ በኩል እየተከናወነ እንደሆነም አክለዋል።

''ለአፍሪካ የምርታማነት ሽግግር የግሉ ዘርፍ ዋነኛ ሞተር መሆን አለበት'' ያሉት ኮሚሽነሩ በግብርና ጥሬ እቃዎች ላይ እሴት በመጨመር ግብርናውንና ኢንዱስትሪውን ማስተሳሰር እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።

የአፍሪካ አገሮች የርስ በርስ የንግድ ልውውጣቸውን ማሳደግ እንዳለባቸውም መክረዋል።

በህብረቱ ትኩረት የተሰጠው የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣናና ነጻ የሰዎች የመዘዋወር መብት የእርስ በእርስ የንግድ ልውውጡን ለማሳደግ የሚያግዝ መሳሪያ እንደሆነም አክለዋል።

የአህጉሩ ማክሮኢኮኖሚ ያለበት ሁኔታ የተሻለ ቢሆንም በርካታ መሰራት ያለባቸው ተግባራት እንዳሉም  ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም