ኢትዮጵያና ኬንያ የምጣኔ ኃብት ግንኙነታቸውን ማጠናከር በሚችሉበት መንገድ ላይ መከሩ

74

አዲስ አበባ የካቲት 1/2011 የኢትዮጵያና ኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የምጣኔ ኃብት ትብብር ማጠናከር በሚችሉበት መንገድ ላይ መከሩ።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ እና የኬንያው አቻቸው ሞኒካ ጁማ ዛሬ በአዲስ አበባ ተወያይተዋል።

የኬንያና የኢትዮጵያ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለዘመናት ምሳሌ  ሆኖ የቆየ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ወርቅነህ ይህ ግንኙነት የአገራቱን ምጣኔ ኃብት ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ ተጠናክሮ በሚቀጥልበት መንገድ ላይ መወያየታቸውን ነው የገለጹት።

በቅርቡ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ግብዣ በቅርቡ ኢትዮጵያን እንደሚጎበኙም ተናግረዋል።

ሚኒስትሮቹ በአገራቱ መካከል ተጨማሪ የንግድ ልውውጦችና ኢንቨስትመንት በሚስፋፋበት መንገድ ላይም ተወያይተዋል።

እንደዚሁም በአካባቢያዊና በጸጥታ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራትና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ)ን ለማጠናክርም ሀሳብ ተለዋውጠዋል።

በኬንያና በኢትዮጵያ ድንበሮች ጉምሩክና ኢምግሬሽን አሰራርን ወጥ በማድረግ በአንድ ቦታ በጋራ መስራት የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁም ተመልክቷል።

ይህም ለሌሎች አፍሪካ አገራት ምሳሌ እንደሚሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ተናግረዋል።

የኬንያ የውጭ ጉዳይና የካቢኔ ሚንስትር ሞኒካ ጁማ በበኩላቸው አገራቱ ልዩ የሆነና ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸው የአገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር  በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከዶክተር ወርቅነህ ጋርም ክፍለ አህጉራዊና አለም አቀፋዊ ግንኙነትን ለማጠናከር ጠቃሚ ሀሳብ መለዋወጣቸውን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም