የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ተጀምሯል

82

አዲስ አበባ የካቲት 1/2011 ስድስት ቡድኖች የሚሳተፉበት የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በወልቂጤ ከተማ ተጀምሯል።

በመክፈቻው የአምናው የሊጉ አሸናፊ ወልቂጤ ከተማ አማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይንን 66 ለ 65 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የውድድር ዓመቱን በድል ጀምሯል።

በመደበኛው 40 ደቂቃ የጨዋታ ጊዜ የሁለቱ ቡድኖች 65 ለ 65 በሆነ የአቻ ውጤት በመጠናቀቁ አሸናፊውን ለመለየት ተጨማሪ አምስት ደቂቃ እንደተጨመረና በጭማሪው ሰአት ወልቂጤ ጨዋታውን ማሸነፍ እንደቻለ ከኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ፌዴሬሽኑ ከዚህ በፊት ሁሉንም ክለቦች በአንድ ምድብ በማካተት በዙር ያካሄድ የነበረውን የውድድር ፎርማት በ2011 ዓ.ም በመቀየር በሁለቱም ጾታዎች የሚሳተፉት ቡድኖች በሁለት ምድብ ተከፍለው በዙር ጨዋታቸውን እንዲያደርጉ የሚያስችል ፎርማት አዘጋጅቷል።

በዚሁ መሰረት በሴቶች በምድብ ”ሀ ”ወልቂጤ ከተማ፣ አማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይንና ቢጂአይ ኢትዮጵያ የተደለደሉ ሲሆን በምደብ ”ለ ” ደግሞ ጎንደር ከተማ፣ ሀዋሳ ከተማና የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ተደልድለዋል።

በውድድሩ ፎርማት መሰረት በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ በምድብ አንድ ላይ የተደለደሉት ሶስቱ ክለቦች ወደ ወልቂጤ በማቅናት ለሶስት ተከታታይ ቀናት እርስ በእርሳቸው ይጫወታሉ።

ነገ  ቢጂአይ ኢትዮጵያ ከወልቂጤ ከተማ፤  ከነገ በስቲያ አማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይን በተመሳሳይ ከጠዋቱ 3 ሰአት ከ30 ደቂቃ ላይ ይጫወታሉ።

በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ በምድብ ሁለት ያሉት ቡድኖች ጎንደር ላይ ከየካቲት 8 አስከ 10 ቀን 2011 ዓ.ም እርስ በእርስ ጨዋታቸውን እንደሚያደርጉ የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ጥር 17 ቀን 2011 ዓ.ም መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን ቀጣይ መርሃ ግብሮች በሚቀጥለው ሳምንት የሚካሄዱ ይሆናል።

ይህን አዲስ አሰራር መከተል ያስፈለገው ክለቦች ብዙ ውድድሮችን ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ ማካሄድ እንዲችሉ መሆኑን ፌዴሬሽኑ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ በሁለቱም ጾታዎች ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም