ለአማራ ክልል የመብትና የልማት ጥያቄዎች መመለስ ህዝቡ ሰላሙን መጠበቅ አለበት---የክልሉ ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት

88

ባህር ዳር የካቲት 1/2011 የአማራ ክልል የልማት ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኝ ህብረተሰቡ በጎንደርና በተለያዩ አካባቢዎች እየታየ ያለውን ግጭት ነቅቶ ሊከታተለው እንደሚገባ የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የጽፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር  አቶ አሰማኸኝ አስረስ ሰሞኑን በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተከሰተውን የሰላምና መረጋጋት ችግር አስመልክተው ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ እንደገለጹት ጥር 24/2011 ዓ.ም የጸጥታ ችግር በነበረባቸው አካባቢዎች ሰፍሮ የነበረውን 24ኛ ክፍለ ጦር በ33ኛው ክፍለ ጦር ለመተካት በነበረው ክፍተት መካከል የቅማንት ህዝብን የማይወክሉ ታጣቂዎች ጥቃት አድርሰዋል።

በዚህም የቅማንት ህዝብ ኮሚቴ ነን ባይ ጽንፈኞች ከክልሉ ልዩ ሃይል ጋር ባደረጉት የተኩስ ልውውጥ የሰው ህይወት ህልፈትና የንብረት ውድመት መድረሱን ተናግረዋል።

የክልሉን ሰላምና መረጋጋት የማይሹ አካላት ድጋፍ ለዘመናት አብረው በኖሩ የአማራና ቅማንት ህዝቦች መካከል ግጭት የተፈጠረ በማስመሰል ድብቅ አጀንዳዎችን ለማስፈጸም እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ከሳምንታት በፊት ምዕራብ ጎንደርን የግጭት ቀጠና በማድረግ የህይወትና የንብረት ውድመት ያደረሰው ሃይል የክልሉ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ጸጥታውን ማስከበር ሲችል ወደ ማዕከላዊ ጎንደር የጥፋት ተልኮውን ማዞር እንደጀመረ አስረድተዋል።

ጥር 24/2011 ዓ.ም የጀመረው የማዕከላዊ ጎንደር ግጭት እስከ ትናንት ድረስ  የቀጠለ ሲሆን  ችግሩ የተባባሰባቸውም ምስራቅ ደንቢያ ወረዳ፣ላይ አርማጪሆ ወረዳና ጪልጋ አካባቢዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ግጭቱ በሌላ ሃይል የተደገፈ ስለመሆኑ መረጃዎች እየተጠናከሩ እንደሚገኙ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ እነማን ለነማን እየሰሩ እንደሆነ መረጃው ተጠናቅሮ ሲያልቅ ለህዝብ ይፋ እንደሚሆን ተናግረዋል።

ትላንትና ምሽት በጎንደር ከተማ አስተዳደር አዘዞ ከተማ በከብት ማድለቢያ ላይ በተነሳ ቃጠሎ በርካታ ከብቶች እንደሞቱ አስረድተው የአደጋው መንስኤ ተጣርቶ ለህዝብ እንደሚገለጽ ጠቁመዋል።

ከባለፉት ወራት ጀምሮ በደረሰ ግጭት ከ39 ሺህ በላይ ሰዎች ከሁለቱም ወገን መፈናቀላቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ የአንደኛው ወገን ተፈናቃይ በሌላኛው ወገን ቤት መጠለሉና መደበቁ ግጭቱ በሁለቱ ህዝቦች መካከል አለመሆኑን እንደሚያረጋግጥ ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስት ከፌዴራል መንግስት ጋር በመሆን የጸጥታ ሃይልን ያሰማራ መሆኑን ጠቅሰው፣ነገር ግን በእያንዳንዱ ቤት የጸጥታ ሃይል ማቆም ስለማይቻል ህብረተሰቡ እራሱ ዘብ ሊቆም እንደሚገባ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም