የሰሜንና ደቡብ ኮርያ የሰላም ስምምነት አስደስቶኛል--የኢትዮጵያ መንግሥት

209
አዲስ አበባ ሚያዝያ 26/2010 በደቡብና ሰሜን ኮርያ መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት እንዳስደሰተው የኢፌዴሪ መንግስት ገለጸ፡፡ የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ሁለቱ አገራት በቅርቡ ባደረጉት ታሪካዊና ውጤታማ ውይይት  የተፈራረሙት የፓንሙንጆም ድንጋጌ የኢትዮጵያን መንግስት አስደስቷታል፡፡ የሁለቱ ሀገራት ስምምነት በመካከላቸው የሰፈነውን ወታደራዊ ውጥረት ያረግበዋልም ተብሏል፡፡ ኢትዮጵያ የሁለቱ አገሮች ፍጥጫ የሚወገደው በውይይትና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ነው የሚል የጸና አቋም እንደነበራት በመግለጫው ተጠቅሷል። በሁለቱ ሀገራት መካከል የተካሄደው ውይይት ግጭቱን በዘላቂነት አስወግዶ አካባቢውን ከኒውክሌር ነጻ ለማድረግ ትልቅ እርምጃ እንደሆነ ሚኒስቴሩ አስታውቋል። ኢትዮጵያ የፓንሙንጆም ድንጋጌ ደጋፊ እንደሆነች በመጠቆም የጋራ ውይይቱ በሁለቱ አገራት መንግስታትና ህዝቦች መካከል ያለውን መተማመን ከፍ በማድረግ የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች አንድነት ያጎለብተዋል የሚል እምነት እንዳላትም በመግለጫው ተመልክቷል፡፡ የደቡብ ኮርያ ፕሬዝዳንት ሙን ጃኢን እና የሰሜን ኮርያው አቻቸው ኪም ጆንግ ኡን ሚያዚያ 19 ቀን 2010 ዓ.ም ሁለቱን አገራት በሚያዋስነው ፓንሙንጆም ከተማ የፓንሙንጆም ድንጋጌን መፈራረማቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም