አገር አቀፍ የግብር ንቅናቄን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ የሩጫ ውድድር ሊካሄድ ነው

78

አዲስ አበባ  የካቲት 1/2011 በመላው ኢትዮጵያ እየተካሄደ ካለው 'የግብር ንቅናቄ' ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ የሩጫ ውድድር መዘጋጀቱን የገቢዎች ሚኒስቴር ገለጸ።

ደካማ መሰረት ላይ የሚገኘውን የአገሪቱን የግብር አሰባሰብ ሂደት በማጠናከር ዘርፉ በአጠቃላይ አገራዊ ልማት ውስጥ የሚጫወተውን ሚና ለማስፋት አገር አቀፍ የግብር ንቅናቄ የተጀመረው ባለፈው ታህሳስ 12 ቀን 2011 ነው።

በኢትዮጵያ ግብር አሰባሰቡ ከአገራዊ ምርት አንጻር ሲታይ በተለይ ከ2008 ዓም ጀምሮ እየቀነሰ መምጣቱን የገቢዎች ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

በመረጃው መሰረት በ2007 ዓ.ም 13 ነጥብ 4 በመቶ የነበረው የግብር አሰባሰብ እያሽቆለቆለ መጥቶ ባለፈው ዓመተ 10 ነጥብ 7 በመቶ ደርሷል።

ይህም የአገሪቷ ግብር አሰባሰብ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ያመለክታል ነው የተባለው።  

ይህንን ታሳቢ በማድረግ መንግሥት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የግብር ንቅናቄው አንዱ ነው።

ሚኒስትሯ ወይዘሮ አዳነች አበቤ በንቅናቄው ዙሪያ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

እስካሁንም በአዲስ አበባ፣ አማራና ትግራይ ክልሎች ንቅናቄው መጀመሩን ተናግረዋል።    

በአሁኑ ወቅትም ንቅናቄው ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ከየካቲት 10 ቀን 2011 ዓም ጀምሮ ''ግብር ለአገሬ'' በሚል መሪ ሀሳብ የሩጫ ውድድር እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።   

የፓናል ውይይት ማከናወን ሌላው መርሃ ግብር መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሯ፤ በአዲስ አበባ በሚሊኒየም አዳራሽ ''የእምየን ለእምዬ'' በሚል መሪ ሀሳብ የካቲት 17 ቀን 2011 ዓ.ም የሙዚቃ ኮንሰርት እንደሚካሄድ ነው ይፋ ያደረጉት። 

የግብር አሰባሰቡ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ መሆኑን ገልጸው የታክስ አስተዳደርና ስርዓት ዘመናዊ አለመሆን፣ የፖሊሲ ማሻሻዎች ላይ የሚታዩ ክፍተቶች፣ ኀብረተቡ ደረሰኝ የመጠየቅ ባህል ደካማ መሆንና የታክስ ማጭበርበር ከምክንያቶቹ መካከል ናቸው።    

እንደወይዘሮ አዳነች ገለጻ የታክስ እፎይታንና ማበረታቻዎችን መበዝበዝ ፣ተጓዳኝ ከሆኑ የፋይናንስና መንግሥት ዘርፍ ጋር የመረጃ ልውውጥ አለመኖር፣ ሀሰተኛ ደረሰኝና የኀብረተሰቡ ንቃተ ህሊና አለማደግ ለታክሰ አሰባሰቡ መዳከም ሌሎች ችግሮች ናቸው።  

መንግሥት በግብር አሰባሰቡ ላይ ውጤታማ ለመሆን የታክስ ስርዓት ትራንፎርሜሽን እያከናወነ  ሲሆን ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።   

በተለይም የገቢዎች ሚኒስቴር ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የ5 ዓመት ታክስ  ሥርዓት ትራንፎርሜሽን መርሃ ግብር እየተተገበረ መሆኑንም አመልክተዋል።    

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተገኙበት ይፋ የሆነው የግብር ንቅናቄ ለአንድ ዓመት የሚቆይ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም