በምስራቅ ጎጃም ዞን በሐሰት የትምህርት ማስረጃ ሲሰሩ የተገኙ 120 በላይ ግለሰቦች በሕግ እየተጠየቁ ነው

80

ደብረ ማርቆስ የካቲት 1/2011 በምስራቅ ጎጃም ዞን በሐሰት የትምህርት ማስረጃ ሲሰሩ የተገኙ 120 ሠራተኞች በሕግ እየተጠየቁ መሆኑን የዞኑ ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ይትባረክ አወቀ እንዳስረዱት በዞኑ የመንግሥት ተቋማት በሐሰት የትምህርት ማስረጃ ተቀጥረው በመሥራት ላይ የነበሩት ሠራተኞች ክስ ተመስርቶባቸዋል።

መምሪያውን ጉዳዩን  ለአማራ ክልል የሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን በመረጋገጡ ለሕግ እንዲቀርብ መወሰኑንም ተናግረዋል።

መንግሥት ሠራተኞቹ መካከል 10 የሚሆኑት የወረዳና የቀበሌ አመራሮች መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የግለሰቦቹ  ጉዳይ በመንግሥት በምህረት ወይም ይቅርታ መመሪያ እንደማይካተትም  አቶ ይትባረክ አስረድተዋል።

ግለሰቦቹ የያዙት ማስረጃ ትክክለኛ ያልሆነ የትምህርት ዝግጅት እንዳላቸው ከማሳየቱም በላይ፣ አግባብ ያልሆነ የደረጃ እድገት፣ዝውውርና ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ሲያገኙበት ነበር ብለዋል።

በሐሰት ማስረጃው ያገኙት ገንዘብ ሥራ ላይ ከዋለ ጊዜ አንስቶ ለማስመለስ  በፍትሐ ብሔርና  በወንጀለኛ መቅጫ ሕጎች ክስ እንደሚመሰረት ኃላፊው አስረድተዋል።

ሠራተኞቹ በማስረጃው ሥራ ተቀጥረው ከሆነ ከሥራ ይባረራሉ። በማስረጃው የደረጃ እድገትና ዝውውር አግኝተውበት ከሆነ ደግሞ አስቀድመው ወደነበሩበት የሥራ መደብ  ይመለሳሉ ብለዋል።

የደብረማርቆስ ከተማ የቀበሌ07 ነዋሪ አቶ የማነ አድማሱ በሰጡት አስተያየት መንግሥት በሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ይዘው ያለችሎታቸውና በማይመጥናቸው ቦታ የተቀመጡትን  ሠራተኞችን ማጥራቱ  ለጉዳዩ የሰጠውን ትኩረት ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ገልጸዋል።

የአንበር ከተማ ነዋሪ አቶ ስለሺ ይስማው በበኩላቸው መንግሥት ሐሰተኛ ትምህርት ማስረጃን የማጣራት ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠውና በጥልቀት ሊመለከተው ይገባል ብለዋል።

በዞኑ ከ1ሺህ 300 በላይ የመግሥት ሠራተኞች በሐሰት የትምህርት ማስረጃ ሥራ ተቀጥረዋል የሚል ጥቆማ እንደደረሰው መምሪያው ይገልጻል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም