ኤጀንሲው ለአርሶ አደሩ ምርቶች የገበያ ትስስር እየፈጠረ መሆኑን ገለጸ

73

ጎባ የካቲት 1/2011 የኦሮሚያ ገበያ ልማት ኤጀንሲ የአርሶ አደሩ ምርቶች ተገቢ ዋጋቸውን እንዲያገኙ ለገበያ ትስስር ላይ ትኩረት ሰጥቻለሁ አለ፡፡

በባሌ ዞን የፓስታና መካሮኒ ስንዴ ምርት የተሻለ ልምድ ያላቸው አርሶ አደሮች ማሳ ጉብኝትና በዘርፉ ተግዳሮቶች ላይ ምክክር በባሌ ሮቤ ተከናውኗል፡፡

የኦሮሚያ ገበያ ልማት ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ገመቺስ መላኩ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት መንግሥት አርሶ አደሮች ገበያን ማዕከል አድርገው ለሚያወጧቸው ምርቶች ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኙ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ ነው፡፡

በዚህም አርሶ አደሩ የሚያነሳውን የገበያ እጦት ጥያቄ ከግምት ውስጥ በማስገባት አርሶ አደሩን፣ የዱቄት ፋብሪካዎችንና የምግብ ፋብሪካዎችን በማገናኘት የገበያ ትስስሩን ለማጠናከር ጥረቱ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡

''አርሶ አደሩ ጥራት ያለውን ምርት ቢያቀርብም ተገቢውን ዋጋ ባለማግኘቱ የልፋቱን ያህል ተጠቃሚ መሆን አልቻለም'' ብለዋል።

ችግሩ በተለይ የፓስታና መካሮኒ ስንዴን በስፋት በሚያመርቱ የባሌና አርሲ ዞን አርሶ አደሮች ዘንድ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ መቆየቱንም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዱቄት ፋብሪካዎች ማህበር ተወካይ ወይዘሮ ሃይማኖት አስፋው በበኩላቸው መድረኩ አርሶ አደሩና ባለሀብቶችን በቀጥታ በማገናኘት በዘርፉ የሚታየውን የተንዛዛ የደላላ ሰንሰለት ከማስቀረት ባሻገር፤ በጥራት ረገድ ያለውን ችግርን ያቃልላል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።

በዞኑ ለፓስታና መካሮኒ ግብዓትነት የሚውል ስንዴ በአራት የአርሶ አደሮች ኅብረት ሥራ ዩኒዬኖች በኩል ግዢ እየተፈጸመ መሆኑንና እስካሁንም 191ሺህ 700 ኩንታል ስንዴ መገዛቱን የተናገሩት የባሌ ዞን የገበያ ልማት ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ አንዷለም ግርማ ናቸው፡፡

ዩኒዬኖቹ ከአርሶ አደሩ ላይ የተቀበሉትን ምርት ውል ለፈጸሙ የዱቄት ፋብሪካዎች እንደሚያስተላልፉም ተናግረዋል፡፡

ምርቱን በብዛትና በጥራት ራሱን ችሎ ለፋብሪካ ለሚያቀርቡ አርሶ አደሮች ሁኔታዎች መመቻቸታቸውንም ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

አስተያየታቸውን ከሰጡ የጎሎልቻ ወረዳ ዲንሳ ቀበሌ አርሶ አደሮች መካከል አቶ ሰኢድ አህመድ ከፋብሪካዎች ጋር የተፈጠረው የገበያ ትስስር ምርታቸውን ለመሸጥ ሁኔታዎችን ከማመቻቸቱም በላይ፤ በልማቱ ላይ እንዲበረታቱ  መነሳሳትን እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል፡፡

''አሁን በተፈጠረልን የገበያ ትስስር በቀጣይነት ምርቱን በስፋት በማምረት ራሳችን ቀጥታ ለፋብሪካ በማቅረብ ከዚህ ቀደም በደላሎች ስንነጠቅ የኖረውን ጥቅም ለማግኘት በትኩረት እንሰራለን'' ያሉት ደግሞ የጊኒር ወረዳ አርሶ አደር ሁሴን መሐመድ ናቸው፡፡

በባሌ ዞን በመኸር ወቅት ከ200ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በፓስታና መካሮኒ ስንዴ መልማቱን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ኃብት ልማት ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል፡፡

በዞኑ በ2010/11 ምርት ዘመን በመኽር ወቅት ከለማው ከ350ሺህ ሄክታር መሬት ዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

በዞኑ ታዋቂ የፓስታና መካሮኒ ስንዴ አምራቾች የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ በቅርቡ ማሳቸውን በጎበኙበት ወቅት የገበያ ችግር እንዲፈታላቸው መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም