በጥረት ኮርፖሬት የቀድሞ አመራሮች የክስ ሒደት ላይ ተጨማሪ የ14 ቀን ቀጠሮ ተሰጠ

120

ባህር ዳር የካቲት 1/2011 የባህር ዳርና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት በጥረት ኮርፖሬት የቀድሞ ከፍተኛ አመራሮች ላይ ከክልሉ የስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን በቀረበው ጥያቄ መሰረት የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ።

ፍርድ ቤቱ ዛሬ በዋለው ችሎት አቶ በረከት ስምኦን ኮሚሽኑ ያቀረበው ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮን በመቃወም የተጠረጠሩበትን ወንጀል ለይቶ እንዲያቀርብላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

ተጠርጣሪዎቹ የጥረት ኮርፖሬት የአክሲዮን ድርሻ ሽያጭ በህገ-ወጥ ፈፅመዋል ለተባለው በጥረት የመመስረቻ ደንብ መሰረት ያልተብራራ በመሆኑ ወንጀል ያልሆነን ጉዳይ ወንጀል እንደሆነ አድርጎ ማቅረብ እንደማይገባም ተናግረዋል።

አሁን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞም በአካባቢው የህግ ባለሙያ ለማቆም መቸገራቸውን ጠቅሰው የፍርድ ሒደቱ ሰብዓዊ መብታቸውን በማይጋፋ መልኩ እንዲካሔድ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

የክልሉ ስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽንም የመያዝና የመክሰስ ህገ-መንግስታዊ መብት የሌለው በመሆኑ ፍርድ ቤቱ በኮሚሽኑ የተጠየቀውን የ14 ቀን ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ውድቅ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

የቀድሞው የጥረት ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ታደሰ ካሳ በበኩላቸው "መንግስት ሳናጣራ አናስርም እያለ ፈፅሟችኋል የተባልነውን ወንጀል ሳያጣራ ጠርጥሮ ማሰሩ ተገቢ አይደለም" ሲሉ ተከራክረዋል።

የዳሽን ቢራ ፋብሪካ ጉዳይ በፌዴራል ደረጃ የተመዘገበ በመሆኑ መታየት ያለበት በክልሉ ሳይሆን በፌዴራል ደረጃ ሊሆን ይገባል በማለት ለፍርድ ቤቱ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

የክልሉ ስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ወንጀል መርማሪ በበኩሉ አቶ በረከት ተጠርጥረው የተያዙበት ምክንያት ፍርድ ቤት ሲቀርቡ እንደተገለጸላቸው በማስታወስ ዝርዝር ጉዳዩ ምርመራው ተጠናቆ ክስ ሲመሰረት በመደበኛ የፍርድ ሒደት እንደሚታይ አስረድተዋል።

ግለሰቦቹ የተጠረጠሩበት ወንጀል በመንግስታዊ ድርጅት ላይ ከባድ ጉዳት ማድረስ፣ የህዝባዊ ድርጅት ስራን በማያመች አኳኋን መምራትና ከባድ ጉዳት በማድረስ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው መሆኑንም ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር የማዋሉ ጉዳይም ድርጅቱ ህዝባዊ በመሆኑ ለማየት የሚከለክለው የህግ አግባብ እንደሌለም ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

በቀጣይ ከሚያከናውናቸው ቀሪ ስራዎች ውስጥ የዳሽን ቢራ ፋብሪካ ዱየት ቫሳሪ ለተባለ ኩባንያ ከ50 በመቶ በላይ ድርሻ የተሸጠበት ሰነድ ተጠርጣሪዎቹ ሲመሩት በነበረ ተቋም ባለመገኘቱ የምርመራ ስራውን ውስብስብ እንደሚያደርገውም ጠቁመዋል።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የሚያስረዱ ሰነዶችና የሰው ምስክሮች በተለያየ ቦታ የሚገኙ በመሆናቸውና፣ የዳሽን ቢራ ፋብሪካ ከሽያጭ ጀምሮ የተከናወኑ ተግባራት ኦዲት እየተደረገ በመሆኑ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተጠይቋል።

ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ የክልሉ ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የጠየቀውን ተጨማሪ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ በመፍቀድ ለየካቲት 15/2011 ዓ.ም እንዲቀርቡ ወስኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም