”በጎ ፈቃደኛ የለገሱት ደም ሕይወታችንን ታድጎልናል”-የባህር ዳር ወላድ እናቶች

944

ባህር ዳር የካቲት 1/2011 በጎ ፈቃደኛ የለገሱት ደም ህይወታቸውን እንደታደገላቸው በባህርዳር ከተማ ፈለገ ህይወት ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል ሕክምና የሚከታተሉ ወላድ እናቶች ተናገሩ።

በአማራ ክልል በተጠናቀቀው ግማሽ የበጀት ዓመት ከበጎ ፈቃደኞች ከ22 ሺህ 500 በላይ ዩኒት ደም ተሰብስቧል።

በሆስፒታሉ ሕክምናቸውን በመከታተል የሚገኙ እናቶች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በበጎ ፈቃደኞች የተለገሰው ደም ተጋርጦባቸው ከቆየው አደጋ በማውጣት ሕይወታቸውን አትርፎላቸዋል።

በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ሕይወትን ለመታደግ የጀመሩትን ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

ከምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ የመጡት ወይዘሮ ጥሩ አበጀ በወሊድ ምክንያት አጋጥሟቸው በነበረ የደም መፍሰስ ለአደጋ ተጋልጠው እንደነበር አስታውሰው፣በጎ ፈቃደኞች በለገሷቸው ደም ከሕመማቸው እንዳገገሙ ተናግረዋል።

ከምስራቅ ጎጃም ዞን የቢቸና ወረዳ ወይዘሮ አሞኘች ሀብቴ በበኩላቸው አጋጥሟቸው በነበረው የደም እጥረት ተቸግረው እንደነበርና በተሰጣቸው አምስት ዩኒት ደም ሕይወታቸውን መትረፉን ገልጸዋል።

“በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች የለገሱትን ደም ባላገኝ ኖሮ፤ አሁን በሕይወት አልገኝም ነበር” ብለዋል።

በፈለገ ህይወት ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል አዋላጅ ነርስ  ጌታነህ አጥናፉ በሆስፒታሉ በደም እጥረት ምክንያት የወላድ እናቶችና ህፃናት ሕይወት ያልፍ እንደነበር አስታውሰው፣በአሁኑ ወቅት የበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ቁጥር በመጨመሩ ችግሩ መወገዱን ተናግረዋል።

ኑሮውን በደብረ ማርቆስ ከተማ ያደረገውና የቴክኒክና ሙያ ተማሪው ነቢዩ ዳንኤል ደም መለገስ ከጀመረ ሶስት ዓመታት እንዳስቆጠረ ተናግሯል።

ለዘጠኝ ጊዜ  ደም መለገሱን ያስረዳው ወጣቱ ሌሎችም ደም በመለገስ በአደጋና በወሊድ ወቅት ደም የሚፈሳቸውን ወገኖች ሕይወት እንዲታደጉ ጠይቋል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪው መጋቤ ኩራልኝ ሞገስ በበኩላቸው “በምለግሰው ደም ክቡር የሆነውን የሰው ህይወት ከማትረፍ የበለጠ የሚያስደስተኝ ነገር የለም” ብሏል።

የቅርብ ጓደኛቸው ባለቤት ታመው በሰጡት ደም ህይወታቸው መትረፉን የገለጹት አስተያየት ሰጪው፣ እስካሁን ለ20 ጊዜ ደም መለገሳቸውን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የደም ባንክ አስተባባሪ አቶ አንዳርጌ አጥናፉ በተጠናቀቀው ግማሽ በጀት ዓመት ከበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ከ22 ሺህ 500 በላይ ዩኒት ደም መሰብሰቡን አስታውቀዋል።

ከተሰበሰበው ደም ውስጥ 21 ሺህ 132 ዩኒት ደም ለመንግሥትና ለግል ጤና ተቋማት ተሰራጭቶ ጥቅም ላይ መዋሉን አስረድተዋል።

ይህም ከቀዳሚው ዓመት ጥቅም ላይ ከዋለው ደም ጋር ሲነፃፀር በ2 ሺህ 618 ዩኒት ደም ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል።

የተሰበሰበው ደም በወሊድ ምክንያት ደም ለፈሰሳቸው እናቶች፣ የመኪና አደጋ ለደረሰባቸው ወገኖችና ሌሎች የደም እጥረት ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ጥቅም ውሏል ብለዋል።

የበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ቁጥር መጨመር ሰዎችን ሕይወት ለመታደግ እንዳስቻለ አስተባባሪው አስረድተዋል።

ከለጋሾች የሚሰበሰበው ደህንነቱ የተጠበቀ ደም ለተጠቃሚዎች ለማድረስ ዘጠኝ የደም ባንኮች አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።