ግብርን ለማሳወቅና ለመክፈል የሚያስችል የኤሌክትሮኒክስ አሰራር እየተዘረጋ ነው

97

አዲስ አበባ የካቲት 1/2011የገቢዎች ሚኒስቴር ግብርን ዘግይቶ በማሳወቅና በመክፈል የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቀነስ የኤሌክትሮኒክስ አሰራር እየዘረጋ ነው።

ግብር ከፋዮች የግብር መክፈያ ጊዜ ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት ሲቀር ወደ ግብር መክፈያ ጣቢያ በመሄድ ያልተገባ መጨናነቅ ሲፈጠሩ ይስተዋላል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ግብር ከፋዮች በግብር ማሳወቂያ ወራት የመጨረሻ ቀናት በሚፈጠረው መጨናነቅ ሲስተም ባለመስራትና በሌሎች ችግሮች ለእንግልት ይዳረጋሉ።

በዚህም በወቅቱ ባለመስተናገድና ወረፋ በመጠበቅ ከቀናት በላይ የስራ ጊዜያቸውን እንደሚያጠፉ ነው የተናገሩት።

ከሲስተም አለመስራት በተጨማሪ በሚፈጠር የተገልጋይ ብዛት አገልግሎቱን በሚሰጡ ሰራተኞች በትህትና ያለማስተናገድ ችግር እንደሚታይም ነው ያነሱት።

ለደንበኞች መጉላላትና ለሲስተም መጨናነቅ ምክንያቱ የመጀመሪያው ግብር ከፋዩ በወቅቱ ያለመምጣት መሆኑንም አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።

የግብር ከፋዩ በወቅቱ ግብሩን አለማሳወቅና አለመክፈል ብቻ ሳይሆን መንግስት ዘመናዊ አሰራሮችን ሊዘረጋ እንደሚገባም ግብር ከፋዮች ተናግረዋል።

በገቢዎች ሚኒስቴር የአገር ውስጥ ታክስ ማስተዋወቅ ቡድን መሪ አቶ መስፍን ሽመልስ እንዳሉት ወርሃዊ ታክስ የሚያሳውቁ ግብር ከፋዮች አንድ ወር የመክፈያ ጊዜ ቢኖራቸውም የሚያሳውቁት መጨረሻ ላይ ነው።

እንደ አቶ መስፍን ገለጻ በሚፈጠረው መጨናነቅ ታክስ ከፋዮች በመሰላቸት የማይከፍሉበትና ለቅጣት የሚዳረጉበት ሁኔታ አለ።

ይህንን ችግር ለማቃለል ግብር ከፋዮች ወደ ግብር መክፈያ ጣቢያ ሳይሄዱ ባሉበት ቦታ ሆነው የታክስ ገቢያቸውን የሚያሳውቁበትና የሚከፍሉበት የኤሌክትሮኒክስ አሰራር እየተዘረጋ ነው ብለዋል።

አሰራሩ በከፍተኛ ግብር ከፋዮች ላይ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እየተደረገ ሲሆን በመካከለኛና አነስተኛ ግብር ከፋዮች ላይም ተግባራዊ እየሆነ ነው።

አሰራሩ ግብርን ዘግይቶ በማሳወቅና በመክፈል የሚፈጠሩ ችግሮችን በመቀነስና ግብር ከፋዩን ከቅጣት ኢትዮጵያንም መሰብሰብ ያለባትን ገቢ ከማጣት ይታደጋል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም