የመከላከያ ሠራዊት ሪፎርም ግዳጁን በብቃት ለመፈፀም የሚያስችለው ነው.. ምሁሩ

61

ጅግጅጋ የካቲት 1/2011 የአገሪቱን መከላከያ ሠራዊት ከፖለቲካ ወገንተኝነት በፀዳ  መልኩ ለመገንባት እየተካሄደ ያለው ሪፎርም ግዳጁን በብቃት ለመፈፀም እንደሚያስችለው አንድ ምሁር ገለጹ።

ሰባተኛው የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት ቀን በጅግጅጋ ከተማ ትናንት በፓናል ውይይት ተከብሯል።

የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ ይትባረክ ንጉስ ለውይይቱ ባቀረቡት መነሻ ጽሁፍ እንዳመለከቱት ሪፎርሙ ሠራዊቱን ለሕገ መንግሥቱ ታማኝና የአገርን ሰላም የሚያስከብርበትን ተልዕኮ በገለልተኝነት ለመወጣት ያግዘዋል።

በዚህም "ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን ከማሳየቱም በተጨማሪ ሁሉም ሕዝቦች 'የኔ ሠራዊት ነው' የሚልበት ጊዜ ላይ ደርሰዋል"።

ሠራዊቱ በሕዝቦች መካከል የሚነሱ ግጭቶች ለመፍታት እያደረገ ያለው ጥረትም የሕዝባዊነቱ መገለጫ እንደሆነም  ምሁሩ ገልጸዋል።

የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብዲፈታህ ሐጂ ቢሒ ሠራዊቱ አገራዊ የለውጥ ሥራዎችን በማገዝ በተለይም  ግጭቶችን በመከላከል እየፈጸመ ያለው ተግባር የሚያኮራ ነው ብለዋል።

ሠራዊቱ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የአንድነት ተምሳሌትና ኅብረ ብሔራዊነትን ተላብሶ ግዳጁን እየተወጣ በመሆኑ ኅብረተሰቡ ከጎኑ ሊቆም ይገባል ያሉት ደግሞ የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት አቶ ኤልያስ ዑመር ናቸው።

የ13ኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ኮሎኔል አሊጋዝ ገብሬ እንዳሉት ሠራዊቱ ሕገ መንግሥታዊ ተልዕኮውን ከማሳካት በተጓዳኝ በአካባቢው የሚከሰቱ ግጭቶችን በመፍታትላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የውይይቱ አንዳንድ ተሳታፊዎች  በሰጡት አስተያየት ሠራዊቱ ከሕዝብ አብራክ የተፈጠረና ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን በተግባር ያስመሰከረ የሰላም ኃይል መሆኑን ከተማ የተከሰቱ ችግሮች የፈታበት ሂደት ማሳያ ነው በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

ሰባተኛው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መከላከያ ሠራዊት በዓል የካቲት 7 ቀን 2011 በአዳማ ከተማ ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም