ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከለውጡ እኩል እየተራመዱ ነውን?

849

የኢትዮጵያ መንግስት አወዛጋቢ ሆኖ ሁለት አስርት ዓመታት የዘለቀውን ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አሰራር ለማስተካከል እርምጃ እየወሰደ ነው።

ተቋሙን ነፃና ገለልተኛ ለማድረግ ከተወሰዱት እርምጃዎች መካከል የቀድሞዋ ፖለቲከኛና ዳኛ ወይዘሪት ብርቱኳን ሚደቅሳ የቦርዱ ሰብሳቢ ተደርገው መሾማቸው አንዱ ነው።

ይህም በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ በዜጎች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን አግኝቷል።

ሰብሳቢዋም ኃላፊነቱን መረከባቸውን ተከትሎ የተለያዩ የማስተካከያ እርምጃዎችን መውሰድ ከጀመሩ ጥቂት ወራት ተቆጥረዋል። 

ሆኖም የአገሪቱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከለውጡ ጋር እኩል እየተራመዱ ያሉ አይመስልም።

ነገሩ እንዲህ ነው።

ዕለተ ረቡዕ በቀን 29/2011 ዓም ከቀኑ ሶስት ሰዓት የምርጫ ቦርድ በጠራው ስብሰባ ላይ የአገር አቀፍ፣ የክልልና በቅርቡ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ከውጭ ወደ አገር የገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ተገኝተዋል።

መድረኩ የሴቶችና የወጣቶች እጥረት ያለበት መሆኑ በግልጽ ይታያል። ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ አመራሮች ውስጥም አንድ ሴት ብቻ ነበር የተገኙት። እርሳቸውም ቢሆኑ ተሳትፏቸው እምብዛም ነበር።

ስብሰባው የተጠራው በተፎካካሪ ፓርቲዎችና በምርጫ ቦርድ መካከል ወደፊት የሚኖረው ግንኙነት የተዋጣለትና የፓርቲዎችን የተናጠል እንቅስቃሴ ገንቢና ስርዓት ያለው ለማድረግ ይቻል ዘንድ በተዘጋጀው የቃል ኪዳን ሰነድ ላይ መምከር ነበር። 

ሰነዱ ሶስት ክፍሎች ያሉት ሲሆን በክፍል አንድ ጠቅላላ የሰነዱ ድንጋጌ፣ በክፍል ሁለት መሰረታዊ ድንጋጌዎች እንዲሁም በክፍል ሶስት ስለ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ስለማቋቋም ያትታል።

የፓርቲዎቹ አመራሮችም ከሰነዱ መግቢያ ጀምሮ የተቀመጡ ነጥቦች ላይ አስተያየት ሰጥተዋል፣ ጥያቄዎችንም አንስተዋል።

ሆኖም ውይይቱ የአስተያየት ድግግሞሽ የበዛበት፣ ከሀሳብ ይልቅ የቃላት ተርጓሜና ሌሎች አላስፈላጊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር።  

አንዱ አመራር ያነሳውን ሀሳብ ደጋግሞ ማንሳት፣ መቃወምና ወሳኝ ባልሆኑ ጉዳዮች ላይ መጠመድም በመድረኩ የተስተዋለው ዋነኛ ተእይንት ነው።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ  የፓርቲዎቹ አመራሮች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣሉ።

ይሁንና ‘ዕድል አልተሰጠንም፣ጥያቄና አካሄድ’የሚሉ ተደጋጋሚ ድምጾች የሰብሳቢዋን ምላሽ ያቋርጣሉ ነበር።

በተለይ በሰነዱ ሶስተኛ ክፍል በተቀመጠው የጋራ ምክር ቤት ማቋቋም ላይ አብዛኛው ፓርቲ ‘መጨመር አለበት፤ መቀነስ አለበት’ የሚሉ ሀሳቦችን አንስቷል።

በሚመሰረተው የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የፓርቲዎች ግንባር ወይም ትብብር እያንዳንዱ ሁለት መቀመጫ አንደሚኖረውና በአገር አቀፍ ፓርቲነት የተደራጁ ደግሞ አንድ መቀመጫ፣ ክልላዊ ፓርቲዎች በበኩላቸው በጋራ በሚመርጡት አንድ ወኪል በምክር ቤቱ እንደሚወከሉ በሰነዱ ተቀምጧል።

ይሁንና አብዛኞቹ የውይይቱ ተሳታፊዎች በዚህ ነጥብ ላይ መግባባትም መስማማትም ባለመቻላቸው ሀሳባቸውን ለምርጫ ቦርድ በጽሁፍ እንዲገልጹና በቀጣይ በሚኖረው ውይይት ላይ እንዲቀርብ  ወይዘሪት ብርቱካን የመፍትሄ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

እንዲያም ሆኖ አብዛኞቹ ፓርቲዎች ሀሳቡን የተቀበሉት አይመስልም።  ምርጫ ቦርድ ሆቴሉን የተከራየው እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት በመሆኑ የፓርቲዎቹ አመራሮች ባለመስማማትና ባለመግባባታቸው ጉዳዩ በጊዜ ገደብ በቀጠሮ ተበትኗል።