የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ተስተካካይ ጨዋታዎች በሦስት ከተሞች ተካሂደዋል

58

ባህር ዳር/ጅማ/መቀሌ ጥር 30/2011 የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ተስተካካይ ጨዋታዎች ዛሬ በሦስት ከተሞች ተካሂደዋል።

በትግራይ ስታዲዬም የተጫወቱት መቐሌ 70 እንደርታ ፋሲል ከነማን  አንድ ለባዶ አሸንፏል።

መቀሌ 70 እንደርታ ሁለት ቀሪ ተሰተካካይ ጨዋታዎች እያሉ ዛሬ ባስቆጠራት ግብ ሶሰት ነጥብ በማግኘት ፕሪሚዬር ሊጉን እየመራ ካለው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር እኩል ነጥብ ይዟል።

አማኑኤል ገብረሚካኤል በ54ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተመታችን ኳስ ወደ ግብ በመቀየሩ ክለቡ ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዞ ወጥቷል።

የፋሲል ተጨዋታዎች በ42ኛውና  በ75ኛው  ደቂቃዎች ላይ ያደረጓቸው ጥሩ ግብ ሙከራዎች በተጋጣሚያቸው ከሽፈዋል።

ኢንተርናሽናል አልቢትር  ለሚ ንጉሤ አራት ተጫዋቾች በፈፀሟቸው ጥፋቶች ቢጫ ካርዶች አሳይተዋል።

የፋሲል ክለብ  አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በሰጠው አስተያየት ጨዋታውን አጥቅተው ቢጫወቱም ግብ ለማስቆጠር ሳንችል ቀርተናል ብለዋል።

የመቐሌ 70 እንደርታ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በበኩሉ ጨዋታው ጠንካራ ፉክክር እንደበረበት ገልጸው፣ አሸንፈው መውጣታቸው ግን እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።

በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲዬም ባህርዳር ከነማ ስሁል ሽሬ ጨወታ በተገናኙበት ጨዋታ ባህርዳር ከነማ ሁለት  ለባዶ አሸንፏል።

ክለቦቹ ባደረጉት ጨዋታም የመጀመሪያውን አጋማሽ ያለምንም ግብ ለዕረፍት ወጥተዋል።

ባህርዳር ከነማ በሜዳውና በደጋፊው ፊት የተሻለ ውጤት ይዞ ለመውጣት ተጭኖ ለመጫወት ባደረገው ጥረትም ድል ቀንቶታል።

በዚህም አጋማሽ ተቀይረው የገቡት በፈቃዱ ወርቁና እንዳለ ደባልቄ ያስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች ባህርዳር ከነማን  ሦስት ነጥብ ይዞ ለመውጣት አስችለውታል።

ጨዋታው ስፖርታዊ  ጨዋነት በተላበሰ መልኩ ተካሂዷል።

ባለሜዳው ጅማ አባጅፋር ለሁለተኛ ጊዜ በሜዳው ላይ ነጥብ የጣለበትን ግጥሚያ አስተናግዷል።

ጅማ አባ ጅፋር ከድሬዳዋ ከተማ በተገናኘበት ውድድር ሶስት ለሶስት በሆነ እኩል ነጥብ ጨዋታቸውን አጠናቀዋል፡፡

ሁለቱም ክለቦቹች ግቦቹን ያስቆጠሩት በመጀመሪያው ግማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ነው፡፡

ድሬዎች  በሰባተኛው ደቂቃ በገናናው ረጋሳ፣ በ13ኛው ደቂቃ ላይ በራምኬሎ ሎክ፣ሶስተኛውን ግብ ደግሞ ፍሬድ ሙሸንዲ በ34ኛ ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል፡፡

ለጅማ አባጅፋር በ24ኛናውና በ44ኛው ደቂቃ ማማዱ ሲዴቤ ያስቆጠረ ሲሆን፤ በመጀመሪያው ግማሽ ማጠናቀቂያ ላይ አስቻለው ግርማ የአቻነቷን ግብ  ማስቆጠር ችሏል።

ድሬዎች ሁሉንም ግቦች ያስቆጠሩት በበረኛው ብቃት ማነስ ነው፡፡

ጅማ አባጅፋር አራት ቀሪ ጨዋታዎች ያሉት ሲሆን፣ተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ  ደግሞ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች ይቀረዋል፡፡

የዛሬውን ውጤት ተከትሎ ባህር ዳር ከተማና ፋሲል ከተማ በተመሳሳይ 21ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው  ስድስተኛና ስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ጅማ አባ ጅፋርድሬዳዋ ከተማ  14 ነጥብ በመያዝ በግብ ክፍያ ተበላልጠው 10ኛና 11ኛ ደረጃ  ይዘዋል፡፡

ስሁል ሽሬ በ11ነጥብ 14ኛ ደረጃ ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም