ኢዜአ አገራዊ መረጃን በፍጥነትና በጥራት ለማቅረብ ዘመናዊ የአሰራር ስርዓትን መከተል አለበት ተባለ

77

አዲስ አበባ ጥር30/2011 የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዜናና ዜና ነክ መረጃዎችን በፍጥነትና በጥራት በማቅረብ ተመራጭ የዜና ምንጭ ለመሆን ዘመናዊ የአሰራር ስርዓትን መከተል እንዳለበት ተገለጸ።

"ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ" በሚል መሪ ሃሳብ ኢዜአ ያዘጋጀው ውይይት ዛሬ ተካሂዷል።

የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት ውይይት ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህር ዶክተር ጌታቸው ድንቁና የኢዜአ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰይፈ ደርቤ ''የኢዜአና የባለድርሻ አካላት ግንኙነት'' በሚል የውይይት መነሻ ጽሁፎችን አቅርበዋል።

በፅሁፎቹ ላይም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ለአገራዊ ልማት ሊጫወት የሚችለው ሚና፣ ያለፈ ታሪክ፣ የገጠሙት ችግሮችና አሁን የደረሰበት ደረጃ ተመልክቷል።

ፅሁፍ አቅራቢዎቹ እንዳሉት ኢዜአ በተለያዩ ጊዚያት የሚፈጠርለት አደረጃጀት ከተቋማት ጋር  ያለው ግንኙነትና ዘመናዊ አሰራረ ለመተግበር በሚያደርገው ጥረት ላይ ተፅእኖ ሲፈጥር ቆይቷል።  

ተቋሙ በቀጣይ ሊሰራባቸው በሚገቡ ጉዳዮችና  ከሌሎች ባለደርሻ አካላት ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር በሚችልበት መንገድ ላይም ፅሁፍ አቅራቢዎቹ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

በዚሁ ጊዜ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎቹ እንደተናገሩት ተቋሙ የመገናኛ ብዙሃንን የመረጃ ፍላጎት ለማርካትና የአገሪቱን መልካም ገጽታ ለማስተዋወቅ በዘመናዊ አሰራር ስርዓት የተቃኘ ዜናና ዜና ነክ መረጃዎችን በፍጥነትና በጥራት ማቅረብ ይጠበቅበታል።

ኢዜአ የተሻለ ባለሙያን በማፍራት፣ ከምስልና ከዜና ይዘት እንዲሁም ከሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ጋር  ተያይዞ የሚነሱ ችግርችን በመፍታት የተወዳዳሪነቱን ጉዞ ማጠናከር እንዳለበትም ነው ተሳታፊዎቹ የጠቆሙት። 

የህዝበ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ ፍትህና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ፎዚያ አሚን እንዳሉት ኢዜአ ዜናና ዜና ነክ መረጃዎችን በፍጥነትና በጥራት በማቅረበ ከተቋማት ጋር ያለውን  ግንኙነት ማጠናከር አለበት።

የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችም ተቋሙ የህዝቡን ፓለቲካዊ፣ ምጣኔ ኃብታዊና ማህበራዊ ፍላጎቶች ለማሟላት በሚያደርገው ጥረት መረጃዎችን ክፍት በማድረግ አገራዊ ሃላፊነትን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ተቋሙም እያካሄደ ያለውን ዘመናዊ ስቱዲዮ ግንባታ ጨምሮ የረጅም ጊዜ  ራዕዩ ላይ ለመድረስ እያከናወና ያለውን ተግባር ማጠናከር አለበት  ሲሉም አሳሰበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ በቀለ ሙለታ በበኩላቸው የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ከድርጅቱ ጋር በጋራ መስራታቸው የተቋማቸውን መረጃ በአንድ ጊዜ ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ለማድረስ ያግዛቸዋል ነው ያሉት።

ባለሙያዎቹ ኢዜአ ለዜናና ዜና ነክ ስራዎች ለመስራት የሚጠይቃቸውን መረጃ በፍጥነት በመስጠት እንዲተባበሩም አቶ በቀለ ጠይቀዋል።

ኢዜአ የተቋማትን የዜና ጥያቄ መሰረት በማድረግ ዜናዎችን በፍጥነትና በጥራት ለማቅረብ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለመተግባር ዝግጅቱን ማጠናቀቁንም አስታውቀዋል።

በውይይቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ቤት መምህራን፣ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችና ሌሎች ተጋባዠ እንግዶች ተገኝተዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ለማጠናከርና ኃላፊነቱን በብቃት መወጣት ይችል ዘንድ በአዲስ መልክ እንዲቋቋም የቀረበለትን አዋጅ በትናንትናው እለት በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል።

ኢዜአ በአገሪቱ ለሚከናወኑ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካ ጉዳዮች ዋነኛ የዜና መረጃ ምንጭ በመሆን ለልማት፣ ዴሞክራሲና የህዝቦችን እኩልነት በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነት አጠናክሮ በማስቀጠል ረገድ ጉልህ ሚና እንዳለው በአዋጁ ላይ ተመለክቷል። 

ኢዜአ የአገሪቱን ገጽታ ለመገንባት የሚጠበቅበትን ሚና መወጣት የሚያስችለውን ተቋማዊና የአሰራር ስርዓት እንዲሁም የተሻለ የህግ ጥበቃ እንዲኖረው ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ስለታመነበትም ነው አዋጁ የወጣው።

ከተመሰረተ 77 ዓመታትን ያስቆጠረው ኢዜአ በኢትዮጵያ ብቸኛው የዜና አቅራቢ የሚዲያ ተቋም ነው።

በአሁኑ ወቅትም አዲስ አበባ ጨምሮ መላው አገሪቱ ባሉት ከ36 ያህል  ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶቹ ባሰማራቸው ጋዜጠኞች አገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ዜናዎች በድምፅ፣ ምስልና ጽሁፍ በማቀናበር በአገሪቱ በሚገኙ የብሮድካስትና ህትመት ሚዲያ ተቋማት አንደዚሁም በራሱ ድረ-ገፅ አማካኝነት ለህዝብ በማሰራጨት ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም