ፕሬዘዳንት ሳህለወርቅ የኢትዮ-ጊኒ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለአህጉራዊ ትብብር የተሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ ነው አሉ

85

አዲስ አበባ  ጥር 30/2011  የኢፌዲሪ ፕሬዘዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የኢትዮ-ጊኒ ግንኙነት ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ማደጉ ኢትዮጵያ ለአህጉራዊ ትብብር የሰጠችውን ትኩረት የሚያሳይ መሆኑን ገለጹ።

ፕሬዘዳንቷ የጊኒ ሪፐብሊክ ፕረዜዳንት ፕሮፌሰር አልፋ ኮንዴን በብሄራዊ ቤተ መንግስት ተቀብለው አነጋግረዋል።

ሁለቱ አገራት ከቅኝ ግዛትና ከነፃነት እንቅስቃሴ ጀምሮ በአፍሪካ ከፍተኛ አስተዋጾ ያደረጉ መሆናቸውን ያነሱት ፕሬዝዳንቷ ትብብራቸውን ማጠናከራቸው ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ከመሰረተችባቸው ጥቂት አገራት መካከል ጊኒ አንዷ  መሆኗን ጠቅሰው ይህም ኢትዮጵያ ለአህጉራዊ ትብብሩ የሰጠችውን ትኩረት  የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በተለይም ኢትዮጵያና ጊኒ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን አቋቁመው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ በሆኑ በ8 ዘርፎች ላይ አብረው ለመስራት መስማማታቸው ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ ነውም ብለዋል።

የጊኒ ሪፐብሊክ ፕሬዘዳንት ፕሮፌሰር አልፋ ኮንዴ በበኩላቸው ጊኒ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ትሰራለች ብለዋል።

ሁለቱ አገሮች በነፃነትና በሌሎች አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ የመሪነት ሚና ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም በአፍሪካና በዓለም አቀፍ  ጉዳዮች ዙሪያ አብረን እንሰራለን ብለዋል።

ኢትዮጵያና ጊኒ በቀድሞዎቹ መሪዎቻቸው በንጉስ ኃይለስላሴ እና በፕሬዚዳንት ሴኮ ቱሬ አማካይነት የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን የአሁኑ የአፍሪካ ህብረትን የመሰረቱ ግንባር ቀደም አገሮች ናቸው።

አገሮቹ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት በ1950 ዓ.ም ሲሆን ጊኒ ሪፐብሊክ ኤምባሲዋን በ1962 ዓ.ም አዲስ አበባ ከፍታለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም