በኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላም ለማምጣት አንድ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ያስፈልጋል ተባለ

92

አዲስ አበባ ጥር 30/2011 በኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላም ለማምጣት ከሚያለያዩ ነገሮች ይልቅ አንድ የሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ማተኮር እንደሚገባ  ተገለጸ።     "

የኢትዮጵያ የሠላም፣ልማትና ዲሞክራሲ ሕዝባዊ የምክክር መድረክ በወቅታዊ አገራዊ የሰላም ጉዳይ ላይ ያተኮረ ውይይት አካሂዷል።     

ለውይይት መነሻ ፅሁፍ ያቀረቡት የመድረኩ አባል ዶክተር መሸሻ ሸዋረጋ "በኢትዮጵያ ለሠላም መሰረት የሆኑ ባህላዊ እሴቶች እየተሸረሸሩ መምጣታቸው አሁን እየታየ ላለው አለመረጋጋት በር ከፍቷል" ብለዋል።  

የሠላም መሰረቱ መግባባት በመሆኑ ይህንን እውን ለማድረግም ከሚለያዩ ጉዳዮች ይልቅ አንድ ለሚያደርጉ ጉዳዮች ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።   

''በተለይ የኛ አገር ፖለቲካ ከሚያስማማ ይልቅ የሚለያዩ ትርክቶች ላይ የተመሰረተ ነው፤ታሪካችንን ለመማር እንጂ ዳግም መቃቃር ለመፍጠር መጠቀም የለብንም '' ሲሉም ተናግረዋል።     

የሠላም ሚኒስትር ደኤታ ወይዘሮ አልማዝ መኮንን በበኩላቸው የሠላምን ባህል መገንባት ከየትኛውም ጊዜ በላይ አሁን አስፈላጊ ነው ብለዋል።

''አሁን ላይ የትኛውም ማህበራዊ ኃላፊነት ሠላም በጸና መሰረት ላይ እንዲቆም ከማድረግ የበለጠ ክብደት ሊሰጠው አይገባም፤ ከዚህ አንጻር ሁላችንም በአንድነት እንድንሰራ ግድ የሚልበት ጊዜ ነውም'' ብለዋል።   

ሠላምና እርቅ ለማምጣት የሚከናወኑ ተግባራት የሚጠበቀውን ውጤት እንዲያመጡም በመከባበር፣በመወያየትና በመተባበር ላይ የተመሰረተ የጋራ ጥረት ማድረግ ወሳኝ እንደሆነ አስረድተዋል።  

''በተለይ በዚህ ወቅት አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድና በውይይት ከመፍታት ይልቅ ፍላጎትን በኃይል የማስፈጸም ዝንባሌዎች እየተስተዋሉ ነው ያሉት ሚኒስትር ደኤታዋ ልዩነቶችን በሰከነ አኳኋን የመፍታት ባህል ሊዳብር ይገባልም ብለዋል። 

የውይይቱ ተሳታፊዎችም በአገሪቷ ዘላቂ ሠላም እንዳይመጣ ምክንያት ያሏቸውን ጉዳዮች አንስተዋል።  

ከሀረሪ ክልል የአገር ሽማግሌ ተወካይ የሆኑት መሀመድ ሀሺም የሕግ የበላይነት ሊከበር ይገባል ብለዋል።  

ከኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የመጡት አቶ አዳነ ከቻሳ እንደሚሉት ደግሞ ዋናው ችግር በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ግጭቶችን በመወያየት የመፍታት ባህል አለመዳበር ነው ብለዋል።

"በአገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች ለሚፈጠሩት ችግሮች ከምክንያት ይልቅ ምልክቶቹ ላይ ትኩረት መሰጠቱ ነው" በማለት የሚሞግቱት ደግሞ የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦነግ) ተወካይ አቶ ቀጄላ መርዳሳ ናቸው።   

ፍትሃዊ የፖለቲካ ተሳትፎ ሳይኖር፣ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ሳይረጋገጥና አንዱ ሌላውን የመግፋት ዝንባሌዎች ሳይፈቱ ሠላም ማምጣት እንደማይቻልም ገልጸዋል።  

እንደ አቶ ቀጄላ ገለፃ መሰል የፖለቲካና ማህበራዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ በአገሪቷ ዘላቂ ሰላም እውን እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል።    

ከአማራ ክልል ምክር ቤት የመጡት አቶ አየሁ ብርሃን በበኩላቸው ከወሰን ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጥያቄዎች ወቅታዊ ምላሽ እየተሰጣቸው አይደልም የሚል ሀሳብ አንስተዋል።

ይህም በተለያዩ አካባቢዎች ሠላም እንዲደፈርስ ምክንያት በመሆኑ ዘላቂ መፍትሄ ያሻዋል ብለዋል።

በውይይቱ ላይ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣የኃይማኖት አባቶች፣የአገር ሽማግሌዎች፣ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አባላትና ታዋቂ ግለሰቦች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም