በአፍሪካ አስገዳጅ የአገር ወሰጥ መፈናቀልን ለመከላከል የመሪዎች ዝግጅት ወሳኝ ነው– ሙሳፋኪ መሐመት

696

አዲስ አበባ ጥር 30/2011 የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳፋኪ መሐመት በአፍሪካ የሚታየውን አስገዳጅ የአገር ወሰጥ መፈናቀል ለመከላከል የአህጉሪቱ መሪዎች ዝግጁነት ወሳኝ መሆኑን ተናገሩ።

ሊቀመንበሩ የህብረቱ 34ኛ የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ መክፈቻ ባስተላለፉት መልእክት “አፍሪካዊያን ስደተኞችን በመደገፍ የዓለም አቀፍ አጋሮች እገዛ እንዳለ ሆኖ እኛም ያላሰለሰ አስተዋፅኦ ማድረግ ይጠበቅብናል” ብለዋል።

የህብረቱ ጉባኤ “አስተማማኝ መፍትሄ በአስገዳጅ ሁኔታ ለሚፈናቀሉ አፍሪካዊያን ስደተኞችና ከስደት ተመላሾች” በሚል መሪ ሃሳብ በመከናወን ላይ ይገኛል።

በአህጉሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩትን ግጭቶችና ፖለቲካዊ ቀውሶች ተከትሎ የሚታየውን መፈናቀል ለማስቆም አፍሪካዊያን በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።

አፍሪካን እ.ኤ.አ በ2020 ከጦር መሳሪያ ቀጠናነት ነጻ ለማድረግ የተያዘው አቅድ በመሪዎቿ የፖለቲካ ቁርጠኝነት መጓደል ሊሳካ እንደማይችልም ሊቀመንበሩ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

በአፍሪካ ቀንድ በቅርቡ እየታየ ያለው ለውጥ እንዲሁም ሰላምና መረጋጋት ጥሩ ማሳያ መሆኑን የጠቀሱት የኮሚሽኑ ሊቀመንበር በዚህ ዙሪያ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የነበራቸውን የላቀ አስተዋጽኦ አድንቀዋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ ቬራ ሶንግዌ በበኩላቸው በአፍሪካ አሁን ላይ 14 ነጥብ 7 ሚሊየን ተፈናቃዮች እንዳሉ የገለፁት ዋና ፀሐፊዋ 7 ነጥብ 3 ሚሊየን ያህል ስደተኞች አሉ ብለዋል።

ከነዚህም ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዙት ተፈናቃዮችና ስደተኞች የምስራቅ አፍሪካ አገራት ዜጎች መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በመሆኑም ከአህጉሪቷ ተፈናቃዮች 59 በመቶ እንዲሁም ከስደተኞች 49 በመቶውን ድርሻ የያዙት ከምስራቅ አፍሪካ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

”ለእድገት የተራበ አህጉር ይዘን የማይናቅ ድርሻ ያለውን የአህጉሪቱን ህዝብ ማግለል የለብንም” በማለትም ዋና ፀሃፊዋ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።