አዲሱ አዋጅ አልኮልን በብሮድካስት ሚዲያ በትኛውም ሰዓት ማስተዋወቅን ይከለክላል

111

አዲስ አበባ ጥር 30/2011 በኢትዮጵያ ማንኛውም ዓይነት የአልኮል መጠጥ በብሮድካስት ሚዲያና በአደባባይ ቢልቦርድ ማስተዋወቅ መከልከሉን የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመደኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ገለፀ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከትናንት በስቲያ ጥር 28 ቀን 2011 ዓም  ባካሄደው ስብሰባ አልኮልን በብሮድካስት ሚዲያ ማስተዋወቅ የሚከለክልና የሲጋራ ማጨሻ ስፍራን የሚገድብ አዋጅ አፅድቋል።

የባለስልጣኑ የጤና ህግ አማካሪ አቶ ደረጀ ሸመልስ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በአዋጁ መሰረት ማንኛውም ዓይነት የአልኮል መጠጥ በየትኛውም ሰዓት በብሮድካስት ሚድያና በየአደባባዩ በሚቆም ቢል ቦርድ ላይ ማስተዋወቅ ተከልክሏል።  

በተጨማሪም ከ21 ዓመት በታች ለሆኑ ታዳጊዎች የአልኮል መጠጥ መሸጥ የተከለከለ መሆኑም ተደንግጓል።

አዋጁ የአልኮል መጠጥን በህትመትና በሶሻል ሚዲያ ማስተዋወቅን ግን አይከለክልም ተብሏል።

ከዚህም ሌላ አዋጁ ትንባሆ በመቶ ሜትር ርቀት ዙሪያ ውስጥ መሸጥ የማይቻልባቸው ቦታዎችን የለየ ሲሆን እነዚህም ትምህርት ቤቶች፣ የወጣት ማዕከላት፣ የህፃናት ማዋያና የመንግስት ተቋማት ናቸው።

ሌሎች ህዝብ የሚሰባሰብባቸው ቦታዎች ላይ ትንባሆ ማጨስ ተከልክሏል ያሉት አቶ ደረጀ የማጨሺያ ቦታ ተብለው የሚከለሉ ቦታዎችም አየር በአግባቡ ሊዘዋወርባቸው የሚችሉ መሆን እዳለባቸውም በአዋጁ ተደንግጓል።

ሲጋራ በነጠላ መሸጥም በአዋጁ ተከልክሏል።

የዓዋጁ መሰረታዊ ዓላማ ህፃናትን ከአጉል ልምዶች በመታደግ መልካም አስተዳደግ እንዲኖራቸው ማድረግ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም