ግብርን በመክፈል አገራዊ ለውጡን ማገዝ ይገባል- የደቡብ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን

97

ሐዋሳ ጥር 30/2011 የንግዱ ማህበረሰብ የሚጠበቅበትን ግብር በወቅቱ በመክፈል የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ እንዲያግዝ የደቡብ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን ጠየቀ።

ክልል አቀፍ የታክስ ንቅናቄ  በወልቂጤ ከተማ ተጀምሯል ።

ባለስልጣኑ ዋና ዲያሬክተር አቶ ንጉሴ አስረስ በወቅቱ እንደገለጹት በግብር አሰባሰቡ ሂደት ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን በመፍታት የክልሉ ኢኮኖሚ የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ መሰብሰብ ትኩረት ተሰጥቷል።

"የክልሉ ህብረተሰብ በተለይም ግብር ከፋዩ የታክስ ስወራና ማጭበርበርን በመከላከል የገቢ አሰባሰቡ ስኬታማ እንዲሆን ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል" ብለዋል ።

''የህዝቡ የልማት ጥያቄ ሊመለስ የሚችለው የንግዱ ማህበረሰብ ገቢውን በማሳወቅ የሚጠበቅበትን ግብር መክፈል ሲችል ነው'' ያሉት ኃላፊው ግብር ከፋዩ ኃላፊነቱን በመወጣት ለውጡን እንዲያግዝ ጠይቀዋል ።

"ተጠቃሚውም ደረሰኝ በመጠየቅ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል" ብለዋል።

በገቢዎች ሚኒስቴር የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ወልደመሰቀል በበኩላቸው "የታክስ ጉዳይ የግብር ሰብሳቢው ተቋም ብቻ ሳይሆን፤ የሁሉም ዜጎች በመሆኑ ህዝቡ ከሚመለከተው አካል ጋር በጋራ ሊሰራ ይገባል" ብለዋል ።

"ስራ አጥ ወጣቶችን የስራ እድል ባለቤት ማድረግና የመሰረተ ልማት ተቋማትን ማስፋፋት የሚቻለው ተገቢውን ገቢ መሰብሰብበ ሲቻል ነው" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ኮሚሽን የሐዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ መርዕድ ናቸው ።

ተገቢውን ግብር ለመሰብሰብ እንዳይቻል የሚያደርጉ በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ የጠቆሙት አቶ ታደሰ ህገወጥ ንግድ፣ የኮንትሮባንድ ታክስ ማጭበርበር ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በገቢና በወጪ ንግዱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያስከተለ ያለውን የኮንትሮባንድ ንግድ ለመከላከል ህዝቡ ከመንግስት ጎን ሊቆም እንደሚገባ አሳስበዋል።

የጉራጌ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪየዞኑ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ታጁ ናስር በበኩላቸው በዞኑ ባለፉት ስድስት ወራት ለመሰብሰብ ከታቀደው 918 ሚሊዮን ብር ውስጥ 362 ሚሊዮን ብር ብቻ መሰብሰቡን ተናግረዋል ።

ግብይትን ያለደረሰኝ ማካሄድ፣ የንግድ ፈቃድን በቤተሰብ ከፋፍሎ ማውጣት፣ የታክስ ስወራና ማጭበርበር ዕቅዱን እንዳይሳካ ያደረጉ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል ።

የወልቂጤ ከተማ የሰላም በር ትምህርት ቤት የታክስ ክበብ አባል ተማሪ አያልነሽ አይተንፍሱ "ግብር ያለ ማጭበርበርና በስርዓት መክፈል አገርን ከድህነት እንድታድግ ያስችላል" ብላለች ።

ግብርን አለመክፈል አገራዊ እድገትን እንደሚጎዳም ገልጻለች ።

''ግዴታዬን እወጣለሁ መብቴን እጠይቃለሁ!”በሚል መሪ ቃል የተጀመረው ክልል አቀፉ የታክስ ንቅናቄ እስከ የካቲት 30 ቀን 2011 ድረስ  ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም