ወላይታ ድቻና መዳወላቡ ዩንቨርስቲ በአፍሪካ ዞን 5 የቮሊቦል የክለቦች ውድድር ይሳተፋሉ

95

ወላይታ ድቻና መዳወላቡ ዩንቨርስቲ በሩዋንዳ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የአፍሪካ ዞን 5 የቮሊቦል የክለቦች ውድድር ኢትዮጵያን ወክለው ይሳተፋሉ።

በአፍሪካ ቮሊቦል ኮንፌዴሬሽን (ሲኤቪቢ) አዘጋጅነት በኪጋሊ ከየካቲት 12 እስከ 17 ቀን 2011 ዓ.ም በሚካሄደው ውድድር ነው፡፡በውድድሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሩዋንዳ፣ከጅቡቲ፣ኤርትራ፣ኬንያ፣ታንዛንያ፣ዩጋንዳ፣ሶማሊያ፣ዩጋንዳና ዞን 5 ውስጥ ከተካተተችው ግብጽ የተወጣጡ 20 ክለቦች  ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል ።

የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌደሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተክሉ ሸዋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት የአፍሪካ ቮሊቦል ኮንፌዴሬሽን (ሲኤቪቢ) አራት የኢትዮጵያ ክለቦች በውድድሩ እንዲሳተፉ ግብዣ አቅርቧል።

በዚሁ መሰረት ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በሐበሻ ሲሚንቶ የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ለሚሳተፉት ስምንት ክለቦች ውስጥ በውድድሩ ላይ የመሳተፍ ፍላጎት ያለው ክለብ ለፌዴሬሽኑ እንዲያሳውቅ ጥሪ ማድረጉን ተናግረዋል።

ጥሪውንም ተከትሎ የአምናው የፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ወላይታ ድቻና መዳወላቡ ዩንቨርስቲ በውድድሩ ላይ እንደሚሳተፉ መግለጻቸውን አመልክተዋል።

ሌሎቹ ክለቦች በበጀት ችግር ምክንያት መሳተፍ እንደማይችሉ በማሳወቃቻው በውድድሩ ላይ የሚሳተፉት ሁለት ክለቦች ብቻ መሆናቸውን አቶ ተክሉ ገልፀዋል።

መዳወላቡ ዩንቨርስቲና ወላይታ ድቻ ለውድድሩ ይረዳቸው ዘንድ ልምምድ መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል የዞን 7 ቮሊቦል የክለቦች ውድድር በማዳጋስካር ከጥር 26 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።

በውድድሩ ተሳታፊ በሆነው በሲሺልሱ ፕራስሊን የሴቶች የቮሊቦል ክለብ የሚጫወቱት ኢትዮጵያውያኖቹ ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች ዮዲት አዲስ እና ፋኖ ከበደ ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑ ታውቋል።

ከትናንት በስቲያ ክለቡ የማዳጋስካሩን ዔምቢቪን 3ለ0 በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ ዮዲት አዲስ ኮከብ ተጫዋች የሚያስብላትን አቋም እንዳያሳየችና ለቡድኑ ማሸነፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከተችና ፋኖም ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ እንዳደረገች ተናግረዋል።

የፕራስሊን ከልብ በውድድሩ የመጀመሪያ ጨዋታ በሞሪሺየሱ ኦሬንጅ ዳማታይት 3 ለ 0 መሸነፉን አስታውሰዋል።

ዮዲት አዲስ እና ፋኖ ከበደ ባለፈው ዓመት በቅደም ተከተል ከነበሩበት የጌታዘሩ ስፖርት ክለብና የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ክለብ ለሲሸልሱ ፕራስሊን ክለብ መፈረማቸውንም አውስተዋል።

የዞን 7 የክለቦች ውድድር የካቲት 3 ቀን 2011 ዓ.ም ይጠናቀቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም