የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በአሰራር ስርዓት ቃል ኪዳን ሰነድ ላይ ባለመስማማት ተለያዩ

98

አዲስ አበባ ጥር 29/2011 የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በአሰራር ስርዓት ቃል ኪዳን ሰነድ ላይ መስማማት ባለመቻላቸው በዝርዝር ለመወያየት ለመጋቢት 15 ቀን 2011 ዓ.ም ቀጠሮ ይዘዋል።

አገር አቀፍ፣ የክልልና ከውጭ የመጡ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚኖረውን ግንኙነትና በተናጠል የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴ የሚገዛ የአሰራር ስርዓት ቃልኪዳን ሰነድ ላይ ዛሬ ሙሉ ቀን ውይይት አካሂደዋል።

ከሰነዱ መግቢያ እስከ የጋራ ምክር ቤት ስለማቋቋም ባሉ ክፍሎች ላይ ነበር ውይይትና ክርክር ሲያካሂዱ የነበረው።

የቃል ኪዳን ሰነዱ ሶስት ክፍሎች ያሉት ሲሆን በክፍል አንድ ጠቅላላ የሰነዱ ድንጋጌ በክፍል ሁለት መሰረታዊ ድንጋጌዎች እንዲሁም በክፍል ሶስት ስለ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ስለማቋቋም በዝርዝር ተቀምጧል።

ለህገ መንግስት ተገዥነት፣ የህግ የበላይነት እንዲከበር የማድረግ ግዴታ፣ ሃይል የመጠቀም ስልጣን የመንግስት ስለመሆኑ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በየትኛውም የአገሪቷ ክፍል እንቅስቃሴ የማድረግ ያልተገደበ ነጻነት፣ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የማድረግ ያልተገደበ ነጻነት በሰነዱ ከተቀመጡ መሰረታዊ ድንጋጌዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ።

የስብሰባዎች፣ ህዝባዊ ሰልፎችና ሌሎች ሁነቶች አፈጻጸም፣ ሚዲያና ማህበራዊ ድረ-ገጾች አጠቃቀምና ነጻነት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ነጻነትና እርምጃ የመውሰድ ግዴታ፣ እንዲሁም የመንግስት ሃብትና ስልጣንን ለፖለቲካ ስራ አለመጠቀምም በሰነዱ የተቀመጡ መሰረታዊ ድንጋጌዎች ናቸው።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በእነዚህ ድንጋጌዎች ላይ ሰፊ ውይይት ካደረጉ በኋላ ይጨመር ወይም ይቀነስ የሚሉ ሀሳቦችን አንስተው ውይይት ተደርጎበታል።

ይሁንና በተለይ በሰነዱ በክፍል ሶስት በተቀመጠው የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ላይ መግባባት ባለመቻላቸው በቀጠሮ መለያየት ግድ ሆኖባቸዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ፓርቲዎቹ በሰነዱ ላይ ይጨመር የሚሏቸውን ያልተካተቱ ሀሳቦች ይዘው እንዲቀርቡ ለመጋቢት 15 ቀን 2011 ዓ ም ቀጠሮ ይዘውላቸዋል።

ይሁንና ውይይቱ በዚህ እንዳይቀጥልና ወደ ዋናው የውይይት አጀንዳ ተገብቶ የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ ምርጫ ቦርድ ዝግጅት ማድረጉን ጠቁመዋል።

በዛሬው የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት ላይ ብዙ ሃሳቦች የተንሸራሸሩበት የጋራ ኮሚሽን ማቋቋምን በተመለከተ ነበር።

ፓርቲዎቹ በዚህ ጉዳይ የሚያነሷቸው በርካታ ሀሳብ እንዳላቸው በመግለጻቸው ሌላ የጊዜ ቀጠሮ ሊያዝ ችሏል።

በውይይት መድረኩ የገዥው ፓርቲ ኢህአዴግን ጨምሮ 103 አገር አቀፍና ክልላዊ ፓርቲዎች ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም