በሶማሌ ክልል የቀድሞው ፕሬዚዳንት አብዲ መሃመድ ዑመር መዝገብ ተከሳሾች ዝርዝር ክስ ይፋ ሆነ

77

አዲስ አበባ ጥር 29/2011 በሶማሌ ክልል የቀድሞው ፕሬዚዳንት አብዲ መሃመድ ዑመር መዝገብ በተጠቀሱ 47 ተከሳሾች ላይ የተመሰረተው ክስ ይፋ ሆነ።

ክስ በተመሰረተባቸው 47 ግለሰቦች መካከል በቁጥጥር ስር ውለው ፍርድ ቤት የቀረቡት ስድስቱ ማለትም አቶ አብዲ ሙሃመድ፣ ራህማ መሀመድ ሀይቤ፣ አብዱራዛቅ ሰኒ፣ አቶ ፈርሃን ጣሂር፣ ጉሌድ አበልና ወርሰሜ ሼህ አብዲ ብቻ ናቸው።

በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራተኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ አቶ አብዲ መሀመድን ጨምሮ ስድስቱ የቀረቡ ሲሆን፤ ከስድስቱ መካከል ለሁለቱ ተከሳሾች አስተርጓሚ ባለመኖሩ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል፤ ቀሪዎቹ ዝርዝር ክሳቸውን አድምጠዋል።

ችሎቱ በቁጥጥር ስር ያልዋሉ ተከሳሾችን ክስ ለማንበብ የፌዴራል ፖሊስ ተከሳሾቹን በቁጥጥር ስር አውሎ እንዲያቀርብ ለየካቲት 20 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በግለሰቦቹ ላይ ከተመሰረቱ 10 ክሶች መካከል አንደኛው ክስ ከ1 እስከ 26 ያሉ ተከሳሾችን ሚመለከት ሲሆን፤ ተከሳሾቹ ለጊዜው ካልተያዙ ግብረ አበሮች ጋር በመሆን በህብረት በማደም በሶማሌ ክልል ከሰኔ እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ቀናት በክልሉ ውስጥ አንዱ ወገን በሌላው ነዋሪ ላይ ጥቃት እንዲፈጽም በማድረግና አለመረጋጋት በመፍጠር መሳተፋቸውን ክሱ ያስረዳል።

በአካባቢው በተለምዶ "ሀበሻ" በሚል በሚጠሩና በክልሉ በሚኖሩ የሌላ ብሄር ተወላጆች ላይ ጥቃት እንዲደርስ በማሰብ በግጭቱ የሚሳተፉ 'ሄጎ' በሚል ስያሜ ወጣቶችን በማደራጀት፣ በገንዘብና ቁሳቁሶች በመደገፍ፣ መሳሪያ በማስታጠቅና ግጭቱ የሚመራበትና መልዕክት የሚተላለፍበት 'ሄጎ ዋሄገን' የሚል የፌስቡክ ገጽ በመክፈት ግጭት ሊያነሳሳ የሚችሉ ይዘት ያላቸው መልእክቶችን እንዲሰራጭ ማድረጋቸውን የክሱ ዝርዝር ያሳያል።

በዚህም በክልሉ ውስጥ የጥቃቱ ዒላማ የተደረጉ 'ነዋሪዎችን መግደል፣ ንብረታቸውንም መዝረፍና ማውደም፣ ባንኮችንና ኢንሹራንሶችን መዝረፍ፣ ቤተክርስቲያናትንና ነዳጅ ማደያዎችን ማቃጠል አለብን' በማለት በየቦታው ተንቀሳቅሰው መልዕክት በማስተላለፍና ትእዛዝ በመስጠት መሳተፋቸው ተመልከቷል።

በተጨማሪም በክልሉ ውስጥ ግጭት እንዲነሳ በማድረግ የሰው ህይወት እንዲጠፋ፣ በመንግስትና በእምነት ተቋማት እንዲሁም በግለሰብ ንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ፣ ሴቶች እንዲደፈሩና በርካታ ሰዎች እንዲፈናቀሉ ማድረጋቸው በክሱ ላይ ተገልጿል፡፡

"በኦሮሞ ተወረናል፣ የኦሮሞ ተወላጆች መሬታችንን ለቀው መውጣት አለባቸው፣ ነዳጃችንን፣ መሬታችንንና ወርቃችንን በጉልበት ሊወስዱብን ነው፣ የፌዴራል መንግስት በህገ ወጥ መንገድ ሊወረን ነው፤ አዲስ መንግስት ለማቋቋም እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፣ ሁላችንም አንድ በመሆን በክልላችን ውስጥ ከሶማሌ ብሄር ውጭ ያሉ ብሔረሰቦችን መግደል፣ ንብረታቸውንም መዝረፍና ማውደም አለብን"የሚል ይዘት ያላቸውና ሌሎች መልዕክቶችም ማስተላለፋቸውን ክሱ ያመለክታል።

ተከሳሾቹ ግጭት በመቀስቀስና በማነሳሳት በሶማሌ ብሔር ተወላጆችና በክልሉ የሚኖሩ ሌሎች ብሔሮች መካከል አለመግባባትና ግጭት እንዲፈጠር አድርገዋል፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አገልጋይ የሆኑ ካህናትና የእምነቱ ተከታይ ግለሰቦች በአሰቃቂ ሁኔታ ቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ በመግደል በእሳት እንዲቃጠሉ ማድረጋቸውም በክሱ ተነስቷል።

በአጠቃላይ ከ59 ሰዎች በላይ ህይወት እንዲጠፋ፣ ከ200 በላይ ሰዎች የአካል ጉዳት እንዲደርስባቸው፣ ሴቶች እንዲደፈሩ፣ 412 ሚለዮን 462 ሺህ 826 ብር በላይ የሚገመት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክት ቤተክርስቲያን፣ የግልና የመንግስት ንብረቶች እንዲወድሙ በጦር መሳሪያ በተደገፈ በማሳመጽና የእርስ በርስ ጦርነት በማነሳሳት ወንጀል ተከሰዋል።

በ2ኛ ክስ ደግሞ ከ27 እስከ 47 የተጠቀሱት ተከሳሾች በተመሳይ ወቅት የዜጎች ተንቀሳቅሶ የመኖርና የመዘዋወር ህገ መንግስታዊ መብት በመጣስ ቀኑ ባልታወቀ ቀን ከሰኔ እስከ ሀምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም "ሄጎ" የሚል ቡድን በማደራጀት፣ መሳሪያ በማስታጠቅና በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ከሶማሌ ውጭ በአካባቢው አጠራር "ሃበሻን መግደል፣ መዝረፍ፣ ንብረት ማውደም፣ ቤተክርስሪያንና ነዳጅ ማደያ ማቃጠል አለብን፣ ይህን ለማድረግ ደግሞ የተደራጀ ጦር አለን" በማለት በመቀስቀስ የወንጀል ደርጊት ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ዘጠኝ የሄጎ ስራ አስፈጻሚ አባላትን በመመልመልና ለእያንዳንዳቸው 100 አባላትን በመምረጥ፣ ጦር መሳሪያ እንዲታጠቁና የግጭት መልክቶችን እንዲያሰራጩ ለሄጎ አባላት ዘመናዊ ሳምሰንግ ስልኮችን በመስጠት ቅስቀሳ አድርገዋል። በአጠቃላይ በመንግስትና በህገ መንግስት ስርዓቱ ላይ አደጋ በመደቀን ወንጀል መከሰሳቸው ተጠቁሟል።

ለግጭቱም ከክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር ወጭ በማድረግ መከፈሉ በክስ ዝርዝሩ ላይ ተጠቅሷል።

በዕለቱ ችሎት ከቀረቡት መካከል የክልሉ ፖሊስ የቀድሞው  ኮሚሽነር ፈርሃን ጣህር በ9ኛ ክስ ላይ የፌዴራል መንግስትን ሰንደቅ ዓላማ በማቃጠል፣ በ10ኛ ክስ ላይ ደግሞ በጅግጅጋ ስፖንጅ ፋብሪካ የጅምላ አደጋ እንዲደርስ ትዕዛዝ በመስጠትና ፋብሪካው ተቃጥሎ ከ58 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ ወንጀል መከሰሳቸው ተጠቅሷል።

አቃቤ ህግ ዝርዝር ክሱን ያስረዱልኛል ያላቸውን 213 የሰው ምስክሮች፣ 23 የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችና ገላጭ የምስል ማስረጃዎችን ከክሱ ጋር ማያያዙ ተመልክቷል።

የተከሳሽ ጠበቆች አቃቤ ህግን የማስረጃ ዝርዝር እንዲደርሳቸው የጠየቁ ሲሆን፤ አቃቤ ህግ ደግሞ የማስረጃ ዝርዝር "ለጠበቆች መድረስ አይገባም" በሚል አቤቱታ በማቅረቡ ችሎቱ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለየካቲት 6 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በነ ጎሃ አጽብሃ መዝገብ በከባድ ሰባዊ መብት ጥሰት ወንጀል ተጠርጣሪዎች ላይ በተጠየቀው የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ችሎቱ ለነገ ከሰዓት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም