በደቡብ ክልል የተከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ውጤታማ እንደነበር ተገለጸ

110

ሆሳእና ጥር 29/2011በደቡብ ክልል ባለፉት ስምንት ዓመታት የተከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ውጤት ማስገኘቱን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ የዘንድሮ የበጋ ወራት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በሐዲያ ዞን ሶሮ ወረዳ ቦና ቀበሌ ትናንት ተጀምሯል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ በዚህ ወቅት እንዳሉት በክልሉ ከ2003 ጀምሮ የተካሄደው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ውጤት ተመዝግቦበታል።

በዚህም የከርሰ ምድር ውሃ  አቅም በማጐልበት  አርሶ አደሩ ከዝናብ ጥገኝነት በመላቀቅ የምግብ ዋስትናውን እንዲያጋግጥ አስችሏል ብለዋል።

ሥራውን ተከትሎ በተካሄደው የተፋሰስ ልማት ወጣቶች በአትክልት ልማት፣በንብ ማነብ፣በእንስሳት ማድለብ ተግባራት መሰማራታቸውን ገልጸዋል።

እንዲሁም የክልሉ የደን ሽፋን  ከ19 ከመቶ ወደ 22 በመቶ መድረሱንም አስታውቀዋል።

የግብርና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ካባ ኡርጌሳ በዚሁ ወቅት ክልሉ ባለፉት ዓመታት ያስመዘገበው ውጤት አበረታች ነው ብለዋል።

ዘንድሮ በሚከናወነው ሥራም ተመሳሳይ  ውጤት እንዲመዘገብበትም እምነታቸውን ገልጸዋል።

በወረዳው የቦና ቀበሌ ነዋሪ አርሶ  አደር ጀካሞ ኢቢሶ በአካባቢያቸው ባከናወኑት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ውጤት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም