በወላይታ ሶዶ ከተማ ዘረፋ የፈጸሙ ግለሰቦች በእስር ተቀጡ

83

ሶዶ ጥር 29/2011 በወላይታ ሶዶ ከተማ ዘረፋ በመፈጸም ክስ የተመሰረተባቸው ሁለት ግለሰቦች በእስር እንዲቀጡ ተደረገ፡፡

አንዳንዴ ሰዎች “ሰው ያስባል ፈጣሪ ይፈጽማል” ሲሉ የደመጣሉ። አባባሉ እኛ ብናስብም ባሰብነው ልክ መዋል አለመዋላችንን የሚያውቀው ፈጣሪ ነው ለማለት ነው። ዛሬ ይህን አከናውኜ፣ እነዚህን ነገሮች ፈጽሜ፣ እዚህ ቦታ ሄጄ የሚሉትንና የመሳሰሉትን እያልን እናስባለን እንጂ ቀድመን ባቀድነውና ባሰብነው ልክ መዋል አለመዋላችንን የሚያውቀው ፈጣሪ ነው። አንዳንዴ እኛ በፈለግነውና ባሰብነው መልኩ መዋላችን ቀርቶ ባላሰብነው መልኩ የምንውልበት አጋጣሚ ስለሚፈጠር ነው ሰዎች ይህን አባባል ሲጠቀሙበት የሚደመጡት።

ሰሞኑን በወላይታ ሶዶ ከተማ በሁለት ግለሰቦች ላይ የደረሰው ገጠመኝ ለእዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። ነገሩ እንዲህ ነው፤ ወይዘሮ አበዙ ለማና አቶ ደረሰ መርዞ የተባሉ ግለሰቦች ጥር 4 ቀን 2011 ዓም በዕለተ ቅዳሜ ከጎፋ ዞን ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት ጉዟቸውን ይጀምራሉ። ወላይታ ሶዶ ከተማ ሲደርሱ እየመሸ በመሄዱ በከተማዋ አድረው ለመውጣት ይወስናሉ፡፡

ከምሽቱ 3፡30 አካባቢ በከተማዋ መሃል ክፍለከተማ ግዶ ቀበሌ በሚገኘው ማሪያም ቤተ-ክርስቲያን አከባቢ የሚያርፉበትን የአልጋ ክፍል ይከራያሉ፡፡ ከዚያ በኋላም ሃገር ሰላም ነው ብለው በጉዞ የደከመ ሰውነታቸውን ለማፍታታትና እራት ለመብላት በሚል አልጋ ከያዙት ቤት ብዙም ሳይርቁ በመንደሩ ታዋቂ በሆነው “ፍቅር ካፌ” አካባቢ ይሄዳሉ።

ሰው ያስባል ፈጣሪ ይፈጽማል እንዲሉ እራት ለመብላትና ዘና ለማለት የሄዱበት አካባቢ ግን ያልታሰበ ነገር ይገጥማቸዋል።  በወንጀሉ የተጠረጠሩ መርሁን ዳርዛና ማሞ ማዳልቾ የተባሉ ግለሰቦች በባለሁለት ጎማ ተሽከርካሪ (ሞተር ሳይክል) መጥተው የወይዘሮ አበዙ ለማን የእጅ ቦርሳ በመንጠቅ ለማምለጥ ይሞክራሉ። በእዚህ ጊዜ ታዲያ አጠገቧ የነበሩት አቶ ደረሰ መርዞ ነጣቂዎቹ እንዳያመልጡ ትግል በማድረጋቸውና የሞተሩን መሪ አለቅም ብለው በመያዛቸው ተያይዘው ከወንጀለኞቹ ጋር ይወድቃሉ፡፡

አቶ ደረሰም በወደቁበት ከፍተኛ ትግል በማድረግ ሞተሩን ያጠፋና ቁልፉን ይነቅላሉ፡፡ ወንጀለኞችም ሞተር ሳይክሉን አስነስተው ማምለጥ እንደማይችሉ ሲያረጋግጡና በአካባቢው የሰዎች ጩኸት እየተበራከተ ሲመጣ ለማምለጥ የሽሽት ሩጫ ይጀምራሉ። 1 ሺህ 660 ብርና 600 ብር ግምት ያለው የሞባይል ስልክና ሌሎች ንብረቶችን የያዘውን ቦርሳ የቀማው አንደኛው ግለሰብ ሲያመልጥ ሞተሩን ሲያሽከረክረው የነበረው ሌላኛ ወንጀለኛ ግን በአካባቢው የነበሩ ነዋሪዎች  አራሩጠው ይይዙታል፡፡

በደረሰው ጥቆማ መሰረት ወደ  አካባቢው የመጣው ፖሊስም ወንጀለኛውን በቁጥጥር ስር ካዋለ በኋላ ተጨማሪ ምርመራ በማድረግ አብሮት የነበረውን ወንጀለኛ እንዲጠቁም ያደርጋል።

ግለሰቡም ጓደኛው መርካቶ ገበያ በተለምዶ ወፍጮ ሰፈር  በሚባል መንደር ከአንድ ግለሰብ ቤት ተከራይቶ እንደሚኖሩ ጥቆማ ይሰጣል፡፡ በራሱ በግለሰቡ መሪነትም ፖሊስ ወደተባለው ቤት ያመራል። ያልተያዘው ወንጀለኛ የቀማውን ቦርሳ ነገሩ ሲረጋጋ ለመውሰድ በሚል እሳቤ እርሱ ብቻ በሚያውቀው ሰዋራ ቦታ በመሸሸግ በቤቱ ውስጥ አገር አማን ነው ብሎ እንደተቀመጠ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ይውላል።

በወንጀለኞቹ ላይ ለፍርድ ቤት የቀረበው የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ፖሊስም ጥር 5 ቀን 2011  የተጠርጣሪዎችን ቃል ተቀብሎ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርዓት መሰረት የክስ መዝገብ አደራጅቶ ለወላይታ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀርባል።

ፍርድ ቤቱ ጥር 6 ቀን 2011ዓም በዋለው ችሎት ግለሰቦቹ በወንጀል ችሎት በተደራጀ መልኩ ሆን ብለው የተሽከርካሪውን የሰሌዳ ቁጥር በመንቀልና ጨለማን ተገን በማድረግ ዘረፋ መፈጸማቸውን የሚገልጽ የክስ ፋይል በእጅ እንዲደርሳቸው ተደርጎ ይነበብላቸዋል።

ግለሰቦቹም ድርጊቱን በመጠጥ ስካር መንፈስ ሆነው መፈጸማቸውንና ስህተት መሆኑን ያምናሉ፡፡ ድርጊቱን የፈጸምነው ጠጥተን ነው በማለታቸውም ይህን ለማረጋገጥ የመከላከያ ምስክር እንዲያቀርቡ ችሎቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ለጥር 20 ቀን 2011 ይሰጣል።

የወላይታ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ መርደኪዮስ ደኣ እንዳሉት በዕለቱ ተጠርጣሪዎቹ የዕምነት ቃላቸውን በመስጠታቸው ምክንያት በእግዚቢትነት የተያዘውና በፖሊስ እጅ የነበረው ገንዘብ፣ የተለያዩ ቁልፎች፣ የሞባይል ቀፎ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሒሳብ ደብተርና የእጅ ቦርሳ ለግል ተበዳዩዋ እንዲመለስ ተደርጎ መንገደኛዋ ጉዟቸውን እንዲቀጥሉ ይደረጋል፡፡

ይሁንና የክስ ሄደቱን ሲመለከት የቆየው የወላይታ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥር 20 ቀን 2011 በዋለው ችሎት ተጠርጣሪዎቹ የመከላከያ ምስክር ማቅረብ እንዳልቻሉና በመጠጥ ምክንያት ሳይሆን ሆን ብለው ድርጊቱን መፈጸማቸውን ከተለያዩ ምንጮች ያረጋግጣል።

አቶ መርደኪዮስ እንዳሉት ሁለቱም ተጠርጣሪዎች በፈጸሙት የወንጀል ድርጊት በመጸጸታቸውና ቀደም ሲል የወንጀል ሪከርድ የሌለባቸው መሆኑን ፍርድ ቤቱ በማቅለያነት ወስዶ እጃቸው ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ በሚቆጠር በሁለት ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኖባቸዋል። ለወንጀል ተግባር የተጠቀሙበት ንብረትም ተሽጦ ለመንግስት ገቢ እንዲሆን ተወስኖ መዝገቡ ይዘጋል፡፡

የወላይታ ሶዶ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ያሊሳ ጋጋ ወንጀሉን የፈጸሙትን ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ለማዋል የነዋሪው በተለይም የሞተር አሽከርካሪዎች ያሳዩት ተሳትፎ ለጸጥታ ኃይሉ ቀጣይ ስራ መነሳሳት የፈጠረ መሆኑን ነው የገለጹት።

ይህን የወንጀል ድርጊት መነሻ በማድረግ ከጥር 17 ጀምሮ የከተማዋን ነዋሪ ያሳተፈ የኦፕሬሽን ስራ በማካሄድ በሦስት ቀናት ውስጥ በተደራጀ መልኩ በተፈጸመ ንጥቂያ፣ ሌብነትና አስፈራርቶ መዝረፍ ወንጀል የተጠረጠሩ ከ23 በላይ ግለሰቦችና ለተግባሩ መፈጸሚያ ከሚጠቀሙባቸው የባለ 2 ጎማ ሞተር ሳይክል ጋር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አመልክተዋል፡፡

ህዝብና የጸጥታ ኃይሉ ባደረገው የተቀናጀ ተሳትፎ የተገኘውን ውጤት አጠናክሮ በማስቀጠል የወንጀል መከላከሉን ተግባር ውጤታማ ለማድረግ የከተማ አስተዳደሩ ቁርጠኛ አቋም መያዙንም ዋና ኢንስፔክተር ያሊሳ አመልክተዋል፡፡ የነዋሪው ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑንም ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም