ከህግ አስከባሪዎች ጋር ተቀናጅተው በመስራታቸው ወንጀሎችን መከላከል እንደቻሉ የገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

61
መተማ  ግንቦት 20/2010 ከህግ አስከባሪዎች ጋር ተቀናጅተው በመስራታቸው በአካባቢያቸው ይፈፀሙ የነበሩ ወንጀሎችን መከላከልና ሰላም ማስፈን እንደቻሉ በምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። በከተማዋ የሰላም ቀንን አስመልክቶ የተዘጋጀ ፌስቲቫል ተካሄዷል፡፡ በፌስቲቫሉ  ከተሳተፉት ነዋሪዎች መካከል የሀገር ሽማግሌው  አቶ ሲሳይ ይመር ለኢዜአ እንዳሉት ከዚህ ቀደም በከተማዋ የተለያዩ ወንጀሎች በስፋት ይፈፀም  ነበር። በከተማዋ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች መጥተው ሰርተው የሚለወጡባት ብትሆንም  በቡድን ተከፋፍሎ የመጣላትና የሰው ህይወት በከንቱ ይጠፋ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማዋ የሰላም ሁኔታ ግንዛቤ በመፍጠርና በሁሉም የፀጥታ ስራ ህብረተሰቡ እንዲሳተፍ በመደረጉ ወንጀሎቹን መከላከልና የአካባቢየቸውን ሰላም ማስከበር እንደቻሉ ገልጸዋል፡፡ "ፖሊስና ህብረተሰቡ በቅንጅት መስራት መቻላቸው  ወንጀልን ቀድሞ መከላከልና ባሉ ጥቃቅን የመልካም አስተዳደር ችግሮች በጋራና በባለቤትነት ስሜት መፍታትና ሰላማችንን ማስጠበቅ ችለናል "ያሉት ደግሞ አቶ ገንዘብ ጀምበር  ናቸው፡፡ ወይዘሮ የሺወርቅ አበባው  በበኩላቸው ሌሊት የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከል በሰፈር አደረጃጀት በመሆን ሴቶች ከወንዶች እኩል ጥበቃ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ " ሰላም በፍላጎትና በምኞች ብቻ አይረጋገጥም " ያሉት ወይዘሮ የሺወርቅ ለሰላም መስፈን በተባበረ መንገድ ሳይሰለቹ በመስራት ሰላምን  ማረጋገጥ እንዳቸሉም ገልጸዋል። ሊቀ ስዩማን ቄስ ገብረስላሴ ኃይለማርያም እንደተናገሩት አሁን በከተማዋ ባለ ጠንካራ የፖሊስ እንቅስቃሴ ወንጀለኞችን ተከታትሎ በመያዝና ለህግ በማቅረብ ድርጊቱን መከላከል ተችሏል፡፡ የተጀመረው የሰላም እንቅስቃሴም በቀጣይ የመንደር አደረጃጀቶቻቸውን አጠናክረው በማስቀጠል ለከተማዋ ሰላም መስፋን የበኩላቸውን ለመወጣት እንደሚሰሩም ነዋሪዎች ገልጸዋል። የገንዳውሃ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢንስፔክተር ኃይማኖት ከፋለ በበኩላቸው የከተማው ነዋሪዎች በ162 የሰፈር አደረጃጀት ተዋቅረው ከህግ አስከባሪዎች  ጎን ሆነው ሰላም የማስጠበቅ ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ ህብረተሰቡ ባካሄደው የሰፈር ጥበቃም ዘንድሮ 38 የቀንድና የጋማ  ከብቶችን ጨምሮ ከ40 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ንብረት ከሌባዎች ማስጣላቸውን ገልፀዋል። በወንጀሉ የተሳተፉ አምስት ተጠርጣሪዎችን በመያዝም ለህግ ማቅረብ ተችሏል፡፡ በተጨማሪም ህገ-ወጥ የሆኑ ሁለት ክላሽ ኮቭ ከመሰል 90 ጥይት ጋርና ሶስት ሽጉጦችም ተይዘዋል፡፡ በዚህም  ባለፈው ዓመት ከነበረው 116 የተፈፀመ ወንጀል ዘንድሮ ወደ 85 ዝቅ ማድረግ መቻሉን የጠቆሙት ኢንስፔክተር ኃይማኖት በቀጣይም ስርዓት የሚያሲያዙ ተግባር  ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። የሰላም ቀንን አስመልክቶ ባለፈው ቅዳሜ  በከተማዋ በተዘጋጀው  ፌስቲቫልም ህብረተሰቡ 102 ሺህ ብር በጥሬ ገንዘብና አንድ ሞተር ሳይክል በመግዛት ለቀበሌ ኮሚኒቲ ፖሊስ አበርክቷል፡፡ በዝግጅቱም የከተማዋ ነዋሪዎች ፣ የህግ አስከባሪዎችና  ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም