የኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህ የቀብር ስነ-ስርዓት ተፈፀመ

141

መርዓዊ ጥር 29/2011 የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል አብራሪ የነበሩት የኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህ የቀብር ስነ-ስርዓት በአማራ ክልል ሜጫ ወረዳ መርዓዊ ከተማ ማህደረ ስብሃት ቅድስት ማርያም ቤተ-ክርስቲያን ተፈፀመ።

በቀብር ስነ-ስርዓቱ ላይ የክልሉን ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ላቀ አያሌውን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የባህርዳርና የሜጫ ወረዳ ነዋሪዎችና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ተገኝተዋል።

የህይወት ታሪካቸው እንደሚያስረዳው ኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህ ሐምሌ 16 ቀን 1944 ዓ.ም በሜጫ ወረዳ መርዓዊ ከተማ ከአባታቸው ከአቶ ሙሉነህ ፈንቴና ከእናታቸው ከወይዘሮ አዛለች ጥሩነህ ተወለዱ።

የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በመርዓዊ እና በባህርዳር ከተማ የተከታተሉ ሲሆን በአየር ኃይል አብራሪነት በዲፕሎማ ተመርቀዋል።

ስልጠናውን እንዳጠናቀቁ የምክትል መቶ አለቃነት ማዕረግ አግኝተው ነበር።

በ1970 ዓ.ም በራሽያ፣ በ1971 ዓ.ም በአሜሪካ በሚግ አብራሪነት የሰለጠኑ ሲሆን በፍልስፍና ሁለተኛ ዲግሪ መያዛቸውንም ታሪካቸው ያስረዳል።

በዚአድባሬ መንግስት የሚመመራው የሶማሊያ ጦር በ1968 ዓ.ም ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህ ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን የሶማሊያ ጦር ካምፕን በመደብደብ በጠላት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ አድርሰዋል።

ኮሎኔል ታደሰ ያበሯት የነበረችውን ተዋጊ ሚግ 23 በጠላት ስትመታም በፓራሹት በመውረድ እጃቸውን ሳይሰጡ ኦጋዴን ከሚገኘው የኢትዮጵያ ጦር ጋር መቀላቀላቸው በህይወታ ታሪካቸው ተገልጿል።

በዚህ የጀግንነት ታሪክም ከኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም የአገሪቱን ከፍተኛ የኮሎኔልነት ማዕርግ ሽልማት አግኝተዋል።

በኢትዮጵያ አየር ኃይል ውስጥ የዕቅድና ፕሮግራም፣ የአየር ኃይል ጥናትና ምርምር ዋና ክፍል ኃላፊና የአየር ኃይል አስተማሪ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን የደርግ ስርዓት ሲወድቅ በጥገኝነት ወደ ኡጋንዳ አምርተዋል።

በኤርትራም በሙያቸው ቆይታ እንደነበራቸውና በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት "ወገኖቼን በአየር አልደበድብም" በማለታቸው ለስምንት ዓመታት መታሰራቸውን ከታሪካቸው ለመረዳት ተችሏል።

የአገሪቱን ለውጥ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ኤርትራ ባመሩበት ወቅት ኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህን በማስፈታት ለአገራቸው አብቅተዋቸው ነበር።

ይሁንና በእስር ላይ በነበሩበት ወቅት ባጋጠማቸው የጤና መታወክ በአገር ውስጥና በህንድ ህክምናቸውን ሲከታተሉ ቆይተው በ67 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

በ1990 ዓ.ም የአርበኞች ግንባርን በመመስረት በሊቀ-መንበርነት ይመሩ የነበሩት ኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህ የሁለት ወንዶችና የአራት ሴት ልጆች አባት ነበሩ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም