አኒሸንት ግሬን የተሰኘው የጤፍ ኩባንያ በሄግ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ተረታ

130

አዲስ አበባ ጥር 29/2011 የኔዘርላንዱ የጤፍ አምራች ኩባንያ (አኒሸንት ግሬን) የጤፍ የአመራረት ሂደትን በተመለከተ ያቀረበው ክስ በሄግ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ውድቅ ተደረገበት።

ኩባንያው በፍርድ ቤት መረታቱ ኢትዮጵያ በቅርቡ በኩባንያው ላይ ክስ ለመመስረት የጀመረችውን እንቅስቃሴ ለማጠናከር እንደሚያግዝ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ገልጿል።

የኔዘርላንዱ የጤፍ አምራች ኩባንያ "ባክልስ" ከተሰኘ የጤፍ አምራች ጋር የጤፍ አመራረት ሂደትን በተመለከተ በባለቤትነት እሰጣ ገባ ውስጥ ገብቶ ቆይቷል።

ኩባንያው የ"ባክልስ" የጤፍ የምርት ሂደት ከኩባንያው ጋር ያላቸውን ሥምምነት በመተላለፍ የተካሄደ መሆኑን አንሰቶ ነው የተከራከረው።

ጉዳዩን የተመለከተው ዘ ሄግ ፍርድ ቤት "ባክልስ" ምንም አይነት ሕግ አለመተላለፉን በማረጋገጥ ኩባንያው ያነሳውን መከራከሪያ ውድቅ አድርጎታል።

ከዚያም ባለፈ ያነሳውን ክስ የጤፍ አመራረቱ ምንም አይነት የጤፍ ባለቤትነትን ማረጋገጫ መብትን መጣሱን እንደማያመላክትም አንስቷል።

ጉዳዩን የተመለከተው የሄግ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤትም የኔዘርላንዱ የጤፍ አምራች ኩባንያ ጥፋተኛ በማለት በይኖበታል።

በዚህም መሰረት ኩባንያው "ባክልስ" 130 ሺ 725 ዩሮ እንዲቀጣ ወስኗል። ይህም በሽርክና ገበያ መሰረት ተፈጻሚ እንዲሆን ውሳኔውን አስተላልፏል።

የክርክር ወጪያቸውንም ሁለቱም የየራሳቸውን ወጪ እንዲሸፍኑም ፍርድ ቤቱ ወስኗል።

ይህን ጉዳይ በተመለከተ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጸው፤ ኢትዮጵያ ጤፍን በተመለከተ ያላትን ሙሉ ባለቤትነት በህግ ፊት ለማረጋገጥ በቅርቡ በኩባንያው ላይ ክስ ትመሰርታለች።

እኤአ በህዳር 2018 ተወስኖ እስከ ትናንት ድረስ ለይግባኝ ክፍት የቆየው ውሳኔ ኢትዮጵያ በኩባንያው ላይ ለመመስረት የምታደርገውን እንቅሰቃሴ ያጠናክረዋል።

ኢትዮጵያ በኩባንያው ላይ ክሰ ለመመስረት የውጪ ባለሙያ መቅጠሯን ነው ጠቅላይ አቃቤ ህግ የገለጸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በጤፍ የባለቤትነት መብት ላይ በተደጋጋሚ ከመዘገቡም በላይ በነጋሪ መጽሄት 1ኛ ዓመት ቁጥር 3 በ2010 ዓ.ም "የልዕለ ጥራጥሬው ምላሽ ያጣ ፈተና" በሚል ርዕስ ሰፊ ዘገባ አውጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም