ደቡብ ወሎ ዞን ከ21 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማሽላ ዘር ተሸፍኗል

53
ደሴ ግንቦት 20/2010 በደቡብ ወሎ ቀድሞ የጣለውን ዝናብ በመጠቀም ከ21ሺህ ሄክታር በላይ የእርሻ መሬት በማሽላ ዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ። በመምሪያው የሰብል ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ አበራ ይመር ለኢዜአ እንደገለጹት በ2010/2011 የምርት ዘምን 441 ሺህ 600 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር ለመሸፈን የሚያስችል  የእርሻ ስራ እየተከናወነ ነው፡፡ ተደጋግሞ ከታረሰው መሬት ውስጥም እስካሁን 21 ሺህ 903 ሄክታር መሬት የተለያዩ ግብዓቶችን በመጠቀም በማሽላ ዘር መሸፈኑን ገልፀዋል። በሚያዝያ ወር የጣለው የበልግ ዝናብ በተለይ ከላላ፣ ለጋምቦ ጃማና በሌሎች የምዕራብ ወረዳዎች ስርጭቱ አነስተኛ ስለነበር የታረሰው መሬት ሙሉ በሙሉ በዘር ሳይሸፈን መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡ አሁን እየጣለ ያለው ዝናብ ስርጭቱ ላልተዳረሰባቸውና በዘር ላልተሸፈኑ አካባቢዎች ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሯል። በዘር ከተሸፈነው ማሳ ውስጥም 9 ሺህ 400 ሄክታሩ በመስመር መዘራቱን ተናግረዋል፡፡ ለምርት ዘመኑ ጥቅም ላይ የሚውል 190 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ዞኑ የገባ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 125 ሺህ ኩንታሉ ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቷል፡፡ ቀሪው ማዳበሪያም በመሰራጨት ላይ ሲሆን ምርጥ ዘር ለማከፋፈል ደግሞ ከአማራ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ የዞኑን ድርሻ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ በደሴ ዙሪያ ወረዳ 039 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር እንድሪስ አራጋው ለመኸር የምርት ዘመን ማሳቸውን ሶስት ጊዜ ደጋግሞ በማረስ ጤፍ፣ ባቄላና ስንዴ ለመዝራት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል። ከግብርና ባለሙያዎች በተሰጣቸው ትምህርት መሰረት ዘንድሮ በተለይ ሩብ ሄክታር በሚሆን መሬታቸው ላይ ጤፍና ስንዴ በመስመር በመዝራት የተሻለ ምርት ለማምረት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል፡፡ በአምባሰል ወረዳ 09 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር መኮነን ሞላ ለመኸር እርሻ ያላቸውን ግማሽ ሄክታር መሬት በቆሎና ማሽላ መዝራታቸውን ጠቁመው አዝመራው በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡ በዞኑ በመኸር ወቅት በተለያዩ ሰብሎች ከሚለማው መሬት 10 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷሏል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም