ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ድንገተኛ ጉብኝት አደረጉ

649

አዲስ አበባ ጥር 29/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ካዛንቺስ አካባቢ የሚገኘውን በገቢዎች ሚኒስቴር መካከለኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ድንገተኛ ጉብኝት አድርገዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው የግብር ከፋዮችን አገልግሎት አሰጣጥ በሚመለከት ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ ከሶስት እስከ 100 ሚሊዮን ዓመታዊ ገቢ ያላቸው አራት ሺህ 482 መካከለኛ ግብር ከፋዮች የሚስተናገዱበት ነው።

በዕለቱ ከተገኙት ተገልጋዮች መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው ግብር ከፋዮች የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።

ተገልጋዮቹ ግብር ለመክፈል በቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ በተገኙበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩም ድንገት በመገኘት የአገልግሎት አሰጣጡን መታዘባቸው የማይጠበቅና አስደናቂ ተግባር ነው ብለዋል።

የቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ብርቱካን ግርማ በበኩላቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ድንገተኛ ጉብኝት መደሰታቸውን ተናግረዋል።

በዕለቱ ተገልጋዮችን ሲያስተናብሩና አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩት ስራ አስኪያጇ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድንገት አጠገባቸው ሲገኙ ማመን እንዳቃታቸው ነው የገለጹት።

አጋጣሚው በዕለቱ የነበሩትን ግብር ከፋዮች እንዲሁም የተቋሙን ሰራተኞች ያስደሰተ እንደነበርም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ግብር ከፋዮች ግብራቸውን እንዲከፍሉ የሚያነሳሳና ለቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱም ከፍተኛ የስራ ተነሳሽነትን የሚጨምር ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ቀደም ሲል በፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግና በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ድንገተኛ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።