60 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብና ወርቅ ከአገር ሊወጣ ሲል ተያዘ

98

አዲስ አበባ ጥር 29/2011 የጉምሩክ ኮሚሽን 60 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የተለያዩ አገራት ገንዘብና ወርቅ ከአገር ሊወጣ ሲል መያዙን አስታወቀ።

ኮሚሽነሩ አቶ ደበሌ ቃደታ በሰጡት መግለጫ ንብረቶቹ የተያዙት በጅግጅጋ ቅርንጫፍ ቶጎ ጫሌ መቆጣጠሪያ ጣቢያ በትናንትናው ዕለት ከሌሊቱ ከ10 እስከ 11 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ነው።

ኮሚሽኑ እያከናወነ ያለው የፀረ-ኮንትሮባንድ ዘመቻ አካል በሆነው በዚህ ተግባር የተለያየ የገንዘብ መጠን ያላቸው አሜሪካ ዶላር፣ ዩሮ፣ ፓውንድና የተለያዩ አገራት ገንዘቦች እና ሰባት ኪሎ ግራም የሚመዝን ወርቅ ነው የተያዘው።

ንብረቶቹን ከአገር ሊያሸሹ የነበሩ አራት ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር ማዋል መቻላቸውን ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።

በቁጥጥር ሥራው ለተሳተፉት የጉምሩክ፣ የፀጥታ አካላትና የአካባቢው ማህበረሰብ ምስጋና የቸሩት ኮሚሽነሩ "ተግባሩ ህገ-ወጦች ከህግ ማምለጥ እንደማይችሉ አንዱ ማሳያ ነው" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም