የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራው የእንስሳት መኖና የመስኖ ልማት ለማከናወን አስችሎናል-የትግራይ አርሶ አደሮች

1061

ማይጨው ጥር 28/2011 የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ የእንስሳት መኖና የመስኖ ልማት ለማከናወን እንዳስቻላቸው የትግራይ ደቡባዊ ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ።

በዞኑ በዚህ ዓመት በሚከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ዕቅድና አፈፃፀም ላይ ያተኮረ ስብሰባ በአዲሽሁ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በስብሰባው ላይ የተሳተፉ አርሶ አደሮች እንደተናገሩት ሥራዎቹ እንስሳት መኖ ልማት ለመሰማራትና የመስኖ ልማትን ለማስፋፋት አስችሏቸዋል።

የአምባላጌ ወረዳ አርሶ አደር ኪሮስ ግርማይ በአካባቢያቸው የተከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በተራራ ግርጌ በሚገኘው የእርሻ መሬታቸው ላይ ይደርስ የነበረውን የአፈር መሸርሸርን እንዳስቀረላቸው ተናግረዋል።

ሥራው የእርሻ መሬታቸውን ለምነት ብሎም የሰብል ምርታማነታቸው እንዲጨምር ማድረጉን ገልጸዋል።

ከአንድ ሄክታር መሬት የስንዴ ማሳ ቀደም ሲል ያገኙት የነበረውን አምስት ኩንታል ምርት ዛሬ ወደ 12 ኩንታል ማድረሱንም ጠቁመዋል።

የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ግደይ ገብረህይወት በበኩላቸው ሥራው የጎርፍ ውሃ ለመጠቀምና የተዳከሙ ምንጮች ለማጎልበት እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።

የአትክልትና ፍራፍሬ በመስኖ በማልማት ከ25 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውንም አስታውቀዋል።

አካባቢያቸው ቆላማ በመሆኑ በበጋ ወቅት የእንስሳት ቀለብ  ተቸግረን ነበር የሚሉት ደግሞ  የራያ አላማጣ ወረዳ አርሶ አደር አሊዩ ከድር ናቸው፡፡የመኖ ተክሎችን በማልማት ችግራቸውን ማቃለላቸውን ተናግረዋል።

በትግራይ ደቡባዊ ዞን ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ ተወካይ አቶ አሰፋ አስረስ ባለፉት ዓመታት በዞኑ በተካሄዱ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች የጎርፍ አደጋ ቀንሷል።የአርሶ አደሮች እንስሳት መኖ ችግር መቃለሉንም  አስረድተዋል።

ከቀጣዩ ወር ጀምሮ በአምስት ወረዳዎች ውስጥ ከ218 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የሚሳተፉበት ሥራ እንደሚጀመር አስታውቀዋል።

በዚህም 8 ሺህ 700 ሄክታር መሬት ላይ ጎርፍ አልባ የተፋሰስ ልማት ይካሄዳል።

በተጓዳኝም ከ20 ሚሊዮን በላይ የበለስ፣ የእሬትና ለእንስሳት መኖ ዝርያዎች ተከላ ይካሄዳል ብለዋል።

በሥራው ለሚካፈሉ ከ14 ሺህ በላይ የቅየሳ ባለሙያዎችና የልማት ቡድኖች ስልጠና መሰጠቱንም ገልጸዋል።