የጊኒው ፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴ ከነገ ጀምሮ የሶስት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት በኢትዮጵያ ያደርጋሉ

90

አዲስ አበባ ጥር 28/2011 የጊኒው ፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴ ከነገ ጀምሮ በኢትዮጵያ የሶስት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደርጋሉ።

ፕሬዝዳንቱ በቆይታቸው ከፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር በአገራቱ የጋራ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ።

በአፍሪካና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያም ውይይት እንደሚያደርጉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጸህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ፕሬዚዳንቱ የካቲት 1 ቀን 2011 ዓ.ም በሚካሄደው የመጀመሪያው የኢትዮ-ጊኒ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ምስረታ ስብሰባ ላይ ይሳተፋሉ።

በአገራቱ መካከል ስትራቴጂያዊ አጋርነት የሚመሰርት የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን የሚቋቋም ሲሆን፣ ዛሬ የኮሚሽኑን ምስረታ አስመልክቶ የኤክስፐርቶች ስብሰባ ተጀምሯል።

ኤክስፐርቶቹ ተወያይተው ያዘጋጁትን ረቂቅ ሰነድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁና የጊኒ አቻቸው ማማዲ ቱሬ ጋር እንደሚፈራረሙም ታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የጊኒው ፕሬዚዳንት አልፋ ኮንዴ በትምህርት ፣በግብርና፣ በባህልና ቱሪዝም መስኮች ለመተባበር የሚያስችል ስምምነቶች ይፈርማሉ ተብሎም ይጠበቃል።

ፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴ በ32ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይም ይገኛሉ ተብሏል።

ኢትዮጵያና ጊኒ በቀድሞዎቹ መሪዎቻቸው በንጉስ ኃይለስላሴ እና በፕሬዝዳንት ሴኮ ቱሬ አማካይነት የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን የአሁኑ የአፍሪካ ህብረትን የመሰረቱ ግንባር ቀደም አገራት ናቸው።

አገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት በ1950 ዓ.ም ሲሆን ጊኒ ሪፐብሊክ ኤምባሲዋን በ1962 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ ከፍታለች።

የሴኔጋል ርዕሰ መዲና ዳካር የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከጊኒ ሪፐብሊክ ጋር የሚካሄደውን የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንደሚያከናውን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም