ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ወራት 9 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የውጭ እዳ ከፈለች

90

አዲስ አበባ ጥር 28/2011 ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ወራት 9 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የውጭ እዳ መክፈሏን የገንዘብ ሚኒስቴር ገለጸ።

መንግስት ያለበትን ከፍተኛ የውጭ እዳ ጫና ለመቀነስ በውጭ ንግድ ላይ የተሰማሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ወደ ስራ በማስገባት የምንዛሬ አቅሙን ለማጎልበት እየሰራ መሆኑም ተገልጿል።

መንግስት አገሪቱ ካለባት አጠቃላይ 26 ነጥብ 791 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እዳ በያዝነው በጀት ዓመት 22 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለመክፈል እቅድ መያዙን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የገንዘብ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሀጂ ኢብሳ የሚኒስቴሩን የስድስት ወር አቅድ አፈጻጸም አስመልክተው በሰጡት መግለጫ  ኢትዮጵያ ያለባትን ከፍተኛ የብድር ጫና ለመቀነስ ጥረት እያደረገች ነው።  

ኢትዮጵያ ካለባት 26 ነጥብ 791 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር እዳ 57 ነጥብ 3 በመቶ የሚሆነው የማዕከላዊ መንግስቱ ሲሆን ቀሪው የልማት ድርጅቶች መሆኑን ገልጸዋል።

እ.አ.አ ከ2015 በፊት ዝቅተኛ የብድር ጫና የነበረባት ኢትዮጵያ ከ2015 አጋማሽ ጀምሮ መካከለኛ የእዳ ጫና ውስጥ እንዲሁም ከታህሳስ 2018 ጀምሮ ከፍተኛ የእዳ ጫና ውስጥ መግባቷን ገልጸዋል።

በመሆኑም መንግስት ካለበት ከፍተኛ የብድር እዳ ጫና ለመላቀቅ በተያዘው በጀት ዓመት 22 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር እዳ ለመክፈል እቅድ መያዙን ገልጸዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ አጋማሽ እስከ ታህሳስ 2011 ዓ.ም 9 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር እዳ በመክፈል በቀጣይ ወራት እቅዱን ለማሳካት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ከሀምሌ 2010 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት አምስት ወራት የወጭ ንግድ 977 ነጥብ 6 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብቻ መሆኑ የአገሪቱን የእዳ ጫና እንዳከበደው ተናግረዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ያለባትን የእዳ ጫና ለመቀነስ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በሙሉ አቅማቸው በማምረት የውጭ ምንዛሬ እንዲያስገኙ ማድረግ ቀጣይ የመንግስት ትኩረት እንደሚሆን አመልክተዋል።

መንግስት 102 የመንግስት ተቋማት ላይ ባደረገው ምርምራ አንድ ሺህ ፕሮጀክቶች ከአንድ እስከ ሰባት ዓመት ድረስ ዘግይተው በመገኘታቸው ከ43 ቢሊዮን ብር በላይ አላስፈላጊ ወጭ እንደወጣ ጠቁመዋል።

በዚህ ምክንያት የሚፈጠረውን የፕሮጀክቶች መዘግየትና የመንግስት ሃብት ብክነት ለመከላከል አፈጻጸማቸውን የሚከታተል "የፕሮጀክቶች አጭር መግለጫ" እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም መንግስት የልማት ድርጅቶችን በሙሉ ወይም በከፊል ወደ ግል ይዞታ ለማዛወር የተለያዩ መመሪያዎችና አደረጃጀቶች እያዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

''ኢትዮ-ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክና የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በከፊል ወደግል ይዞታ እንዲዛወሩ እንቅስቃሴ ተጀምሯል'' ብለዋል።

ኢትዮጵያ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደግል ይዞታ ለማዘዋወር ጀማሪ በመሆኗ ሁሉንም በአንድ ጊዜ ሳይሆን በቅደም ተከተል ለማዛወር በቅድሚያ የኢትዮ ቴሌኮም አሰራሮች እየተፈተሹ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በሂደት መንግስት ውሳኔ ያሳለፈባቸው የመንግስት የልማት ድርጅቶች በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ ወደግል ይዞታ እንዲዘዋወሩ የሚደረግ መሆኑን ጠቁመዋል።

የገንዘብ ሚኒስቴር ባለፉት 100 ቀናት ሊሰራቸው ያቀዳቸው ዋና ዋና ተግባራት የአገሪቱን የገንዘብ ምንጭ ማሳደግ፣ የዕዳ ጫናን መቀነስ፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ወደግል ማዘዋወር እንዲሁም የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም